አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን የተሳሳተ ፖሊሲ እንድታርም የዲፕሎማሲ ጥረት እየተደረገ ነው

204

ታህሳስ 1/2014/ኢዜአ/ በአሜሪካ ሎስአንጀለስ ከተማ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን የተሳሳተ ፖሊሲ እንድታስተካክል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኔትወርክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኔትወርክ፤ የአሜሪካ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አማካኝነት ከአንድ ዓመት በፊት  የተመሰረተ ጥምረት ሲሆን፤ የሲቪክ ተቋማትን፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችንና ሌሎች የተለያዩ ቡድኖችን በስሩ ያቀፈ ነው።

ጥምረቱ በዲፕሎማሲ፣ በሕዝብ ግንኙነት፣ በሃብት ማሰባሰብና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኔትወርክ በአሜሪካ ምዕራባዊ ጠረፍ (ዌስት ኮስት) በሚገኙ 11 ግዛቶች ውስጥ ቅርንጫፎች አሉት።

የኔትወርኩ የሎስ አንጀለስ ቻፕተር ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ደምሴ ለኢዜአ እንዳሉት፡ አባላቱ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና እንድታቆምና የተሳሳተ ፖሊሲዋን እንድታስተካክል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረጉ ነው።

የኔትወርኩ አመራሮችና አባላት በየአካባቢያቸው የሚገኙ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት ጋር ውይይት በማድረግና ደብዳቤ በመጻፍ የኢትዮጵያን እውነታ የማስረዳት ስራ እያከናወኑ ነው ብለዋል።

በሕዝብ ግንኙነት መስኩም ዳያስፖራው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብ የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ ፖሊሲ እየተከተለ ያለው የዴሞክራት ፓርቲ በአካባቢያዊና በአጋማሽ ዓመት(ሚድ ተርም ኢሌክሽን) ለሪፐብሊካን እጩዎች ድምጽ በመስጠት ፖሊሲውን ዳግም እንዲያጤን በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እየተደረገ ባለው የተደራጀ እንቅስቃሴና ጥረት ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት ዳያስፖራው የሚያቀርበውን ሀሳብ ለማዳመጥ፣ ለማናገርና ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት ማሳየት ጀምረዋል ያሉት አቶ በቀለ ይህ መልካም እርምጃ እንደሆነ አመልክተዋል።

የዲፕሎማሲው ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልና አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የወሰደቸው እርምጃ እስኪቀለበስ ያላሰለሰ ጥረት በዳያስፖራው እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና ለመመከት እየተከናወኑ ያሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች መስፋፋት እንዳለባቸውና ዳያስፖራውም የነቃ ፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ነው አቶ በቀለ የገለጹት።

በሎስአንጀለስ ከተማ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ከዲፕሎማሲው ስራ ባለፈ ለወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎችና ለልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በሎስ አንጀለስ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር 640 ሺህ ዶላር መሰብሰቡ የሚታወስ ነው።