ምሁራንና ጋዜጠኞች አህጉራዊ ንቅናቄውን ሊቀላቀሉ ይገባል

77

ጎንደር፣ ታህሳስ 1/2014 (ኢዜአ ) ''አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተገቢውን ውክልና እንድታገኝ በአፍሪካ ታላላቅ መሪዎች የተጀመረውን አህጉራዊ ንቅናቄ ምሁራንና ጋዜጠኞች ሊቀላቀሉት ይገባል'' ሲሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁር ተናገሩ፡፡

በዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አስተምሬ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ተገቢውን ውክልና ሊኖራት ይገባል የሚለውን ንቅናቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በይፋ መቀላቀላቸው አህጉራዊ አሻራቸውን ያሳረፉበት ታሪካዊ ውሳኔ ነው፡፡

የአፍሪካ አህጉር ቋሚ የአባልነት መብት መነፈጉ በተመድ ቻርተር ሉዓላዊ ሀገሮች እኩል የአባልነት መብት አላቸው የሚለውን መርህ በጥብቅ የጣሰ መሆኑን ገልፀዋል።

"አፍሪካ 54 ሀገሮችንና 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ ያቀፈ ታላቅ አህጉር በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖረው መደረጉ ድርጅቱ የምእራባውያን ሀገራት መብት አስጠባቂ ድርጅት እንደሆነ አመላካች ነው " ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካን ጨምሮ በበርካታ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጪ በሆነው የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ አህጉር ቋሚ መቀመጫ እንዲያገኝ ቢደረግ ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን አመልክተዋል።

''በመሪዎች ደረጃ የተጀመረው ንቅናቄ የአፍሪካን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያግዝ ነው'' ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ መሪዎቹ መላውን አፍሪካዊያንን በማነቃነቅ ገፍተው ሊሄዱበት የሚገባ የዘመኑ ታላቅ አፍሪካዊ አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ንቅናቄው የመላው አፍሪካውያን የፍትህና የእኩል መብት ጥያቄ በመሆኑ አፍሪካውያን በድርጅቱ ቋሚ የውክልና መቀመጫ እንዲያገኙ መሪዎች ጥያቄውን አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"የጸጥታው ምክር ቤት የሉአላዊ ሀገሮች ስብስብ ነው ብሎ መውሰድ የሚቻለው በርካታ ሀገራትንና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያለው የአፍሪካ አህጉር ቋሚ የውክልና መቀመጫ ሲያገኝ ብቻ ነው" ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ይህንን በመሪዎች ደረጃ የተጀመረውን ንቅናቄውን በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ምሁራንና ጋዜጠኞች በመቀላቀል የአፍሪካውያን ድምጽ በፀጥታው ምክር ቤት ጎልቶ የሚወጣበትን ታሪካዊ ትግል ከዳር ማድረስ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

" የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካውያን አቤቱታ የሚያቀርቡበት ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ጉዳይ የሚወስኑበት ብሎም ውሳኔዎችንም የሚሽሩበትና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ጭምር ሊያጎናጽፋቸው ይገባል" ብለዋል፡፡  

"ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝን የታገለችና በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ያልወደቀች ነጻ አፍሪካዊ ሀገር እንደ መሆኗ በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካን የሚመለከቱ ጉዳዮችና ውሳኔዎች ያለ አፍሪካውያን ተሳትፎ እንዳይከናወን ንቅናቄውን ማጠናከር አለባት" ሲሉም አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት መስራች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ዛሬም በተመድ ውስጥ አፍሪካ ተገቢውን የውክልና መብት እንድታገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ንቅናቄውን በይፋ መቀላቀላቸው ተገቢና ወቅታዊ መሆኑንም ረዳት ፕሮፌሰሩ ጠቅሰዋል፡፡

በጥቂት የአፍሪካ መሪዎች የተጀመረው ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን የመላው አፍሪካውያን ያልተቋረጠ ሞጋች  የሆነ ትብብርና እገዛ እንደሚያስፈልግ  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም