በውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትንና አላስፈላጊ ጫናን በምርጫ ካርድ የመቅጣት ዘመቻ ተጀመረ

65

ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና አላስፈላጊ ጫና በመፍጠር ላይ የሚገኘውን የባይደን አስተዳደርና የዴሞክራት ፓርቲን በሜሪላንድ በምርጫ ካርድ ለመቅጣት ያለመ ዘመቻ በይፋ ተጀመረ።

የአሜሪካ ኢትዮጵያ ፐብሊክ ጉዳዮች ኮሚቴ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በሜሪላንድ ምርጫ የባይድን አስተዳደርን ለመቅጣት እንቅስቃሴው መጀመሩን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል።

በአውሮፓውያኑ አዲስ አመት 2022 እንደ ባተ በሚካሄደው የሜሪላንድ የመካከለኛ የምርጫ ጊዜ በሚካሄደው ምርጫ ከኮሚቴው ጋር በመሆን ሃያ የኢትዮ-አሜሪካ ማህበረሰብ ጥምረቶችና የቢዝነስ ተቋማት ዘመቻውን እንደሚመሩት በመግለጫው ተመልክቷል።

በዚህ የመካከለኛ ጊዜ የሜሪላንድ ምርጫ ላይ የባይደንን አስተዳደርና የዴሞክራት ፓርቲን ለመቅጣት እንቅስቃሴ ይካሄዳል።

በዚህም ኮሚቴው፣ የኢትዮ-አሜሪካ ማህበረሰብ ጥምረትና አጋር አካላት ቤት ለቤት በመሄድ እንዲሁም ስልጠናዎችን በመስጠት በምርጫው ላይ የማንቃት እንቅስቃሴ እንደሚሰሩም ተገልጿል።

የአሜሪካ ኢትዮጵያ ፐብሊክ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበር መስፍን ተገኑ እንዳሉት ዘመቻው ከሲቪክ ማህበራት ጋር በመተባበር እንዲሁም በጎ ፍቃደኞችን በመቅጠርና ተመሳሳይ አጀንዳ ካላቸው አካላት ጋር ጥምረት በመፍጠር ይመራል ብለዋል።

የኢትዮ-አሜሪካን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የሁለትዮሽ ግንኙነትን አስታውሰው፤ ከአጋር አካላት ጋር በመሆንም ድምጻችንን የሚሰማ አካልን ወደ ስልጣን በማምጣት የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን እንሰራለን ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በቨርጂኒያ የመካከለኛ ጊዜ ምርጫ በግዛቷ የሚገኙ ኢትዮ-አሜሪካውያን የዴሞክራት ፓርቲንና የባይደን አስተዳደርን በምርጫ ካርዳቸው ለመቅጣት ተግባራዊ እንቅስቀሴ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም