የተማሪዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአገር ክብር እና ፍቅር የሚከፈል መስዋዕትነትን በተግባር ያሳየ ነው

66

ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተማሪዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአገር ክብር እና ፍቅር የሚከፈል መስዋዕትነትን በተግባር ማሳየት ያስቻለ ነው ሲል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በሣምንቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ በተለያየ መልኩ መካሄዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከሕዳር 27 ቀን 2014 ጀምሮ በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብል መሰብሰብ፣ ደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጽዳት፣ ዕጽዋት እንክብካቤ እና ሌሎችም ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህም 140 ሺህ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ተማሪዎቹ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንዲገነዘቡ፤ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችላቸው አስተሳሰብ የመገንባትና የማስረጽ ስራ ሲከናወን መቆየቱን አቶ ዘላለም ገልጸዋል።

የአገር መከላከያ፣ ሚሊሻና ልዩ ሃይሎች በግንባር እየከፈሉ ያለውን መስዋዕትነት በተጨባጭ እንዲያውቁ መደረጉንም ተናግረዋል።

ይህም ለተማሪዎች ለአገር ፍቅርና ክብር ስለሚከፈል መስዋዕትነት በማስገንዘብ ትልቅ ውጤት የተገኘበት እንደሆነ ነው ያወሱት።

ይህም ብቻ ሳይሆን የሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አገር ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት በመሆኑ እነርሱም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱበት ነው ብለዋል።

ተማሪዎች ስለ አገራቸው፣ ስለ አንድነት፣ ስለተከፈለላቸው ዋጋ በተግባር በዓይናቸው ያዩበት ዘመቻ እንደነበር ጠቅሰው በቀጣይ መሰል መርሃ ግብር እንዲኖር ልምድ የተወሰደበት መሆኑንም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ጠንካራና የማትሸነፍ አገር ሆና እንድትቀጥል ተማሪዎች ከእነሱ የሚጠበቀው ኃላፊነት በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል ነው ያሉት የቢሮ ሃላፊው።

በሌላ በኩል ለሠራዊት አባላት ከትምህርት ማኅበረሰቡ የተሰበሰበ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ መደረጉን አቶ ዘላለም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም