በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የትምህርት ተቋማት መልሰው ለአገልግሎት እንዲበቁ በቁርጠኝነት ይሰራል

63

ባህር ዳር ታህሳስ 1/2014--(ኢዜአ) -አሸባሪው የህወሓት ቡድን ያወደማቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ በመገንባትና በመጠገን ለአገልግሎት ለማብቃት መንግስት በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ ።

በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ የወደሙ ከ4ሺህ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ያወደማቸው የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በውይይቱ ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ በሚቀረፅባቸው የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።

ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የወደሙና የፈራረሱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባትና በመጠገን ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የትምህርት ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር በሚደረገው ርብርብ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

"የፈረሱት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት እንዳይሆኑ  የጥራት ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ ገንብቶ ለአልግሎት ማብቃት የግድ ነው" ብለዋል።

"ተቋማቱ በጥራት ተገንብተው ለአገልግሎት ካልበቁ የአሸባሪውን ዕቅድ ማሳካት ስለሆነ የመልሶ ግንባታና ማደራጀቱ ሥራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል" ሲሉም አክለዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማተቤ ታፈረ በበኩላቸው እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በቆዩ የክልሉ አካባቢዎች ከ4ሺህ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን አውድሟል።

ትምህርት ቤቶች ገንብቶና ጠግኖ መልሶ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ሃላፊዋ እንዳሉት ትምህርት ቤቶቹ በመውደማቸው ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲሁም 116 ሺህ መምህራን ከሥራ ውጭ ሆነዋል።

የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባትና ቁሳቁስ አሟልቶ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ ዶክተር ማተቤ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም