በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ከአምስት ወራት በላይ ሰብዓዊ ድጋፍ አጥተው ሲቸገሩ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ዝምታ መርጠዋል

83

ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት ወረራ በፈፀመባቸው ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና ዋግኸምራ ዞኖች ከአምስት ወራት በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አጥተው ሲቸገሩ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ዝምታ መምረጣቸው አሳዛኝ መሆኑን የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

አሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአንዳንድ ዓለም አቀፉ የማኅበረሰብ አካላት አለመወገዛቸውም አስገራሚ ሆኗል ብሏል።

የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ ጋር በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፤ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላም ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን አስታውሰዋል።

ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታውን ለማሳለጥ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

በሦስት ኮሪደሮች በመጠቀም ወደ ክልሉ የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ መደረጉንና ከአዲስ አባበ ወደ መቀሌ የአየር ትራንስፖርት ተፈቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም አቶ ምትኩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የፍተሻ ጣቢያዎችን ከሰባት ወደ ሁለት በመቀነስ፤ የሠብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች የሚሰጠውን የቪዛ ቆይታ ጊዜ ከአንድ ወር ወደ ሦስት ወር ማራዘም ተችሏልም ነው ያሉት።

የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የጉዞ መረጃ (የይለፍ) ሰነዶች የማዘጋጀትና የግንኙነት መሳሪያዎች እውቅና የመስጠት ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል።

ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚያግዝ ገንዘብ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ እንዲደርስ በማድረግ መንግስት እየሰራ ቢሆንም አንዳንድ አካላት ግን ጥረቱን እውቅና መስጠት አልፈለጉም ብለዋል አቶ ምትኩ።

በአንጻሩ የሕውሃት ቡድን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን እየጣሰ፤ በዜጎች ላይ አሰቃቂ ወንጀል እየፈፀመ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቋማት ዝምታን መርጠዋል፤ ሲያወግዙትም አይታይም ነው ያሉት።    

የሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው ወደ መቀሌ ከገቡት 1 ሺህ 317 የጭነት ተሽከርካሪዎች መካከል 1 ሺህ 10ሩ ወይም 77 በመቶው እስካሁን አለመመለሳቸውን ጠቁመዋል።

እርዳታ ጭነው ወደ መቀሌ የገቡ ተሽከርካሪዎችን ወረራ ለመፈፀም ታጣቂዎችን እያመላለሱ ቢሆንም ቡድኑ በዚህም ድርጊቱ እየተወገዘ አይደለም ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ሰብአዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ጭነታቸውን አራግፈው ለመውጣት ከ3 እስከ 5 ቀናት ብቻ የሚወስድባቸው ቢሆንም በቅርቡ ወደ ክልሉ ምግብና ምግብ ነክ ሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው የገቡት 203 ተሽከርካሪዎች እስካሁን አለመመለሳቸውን ጠቁመዋል።  

አሸባሪው ሕወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈፀመባቸው አከባቢዎች 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች እንደተፈናቀሉና 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።

ቡድኑ በርካታ የህዝብ መገልገያዎችንና መሰረተ ልማቶችን ከማውደም በተጨማሪ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ ፈፅሟል ብለዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች እንዳይገባ ከልክሎ ሳለ አጋር አካላት ይህንን እኩይ ተግባር ለማውገዝ አልደፈሩም ነው ያሉት።

አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በገባባቸው ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና በዋግኸምራ አካባቢዎች ከአምስት ወራት በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አጥተው ሲቸገሩ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ዝምታ መምረጣቸው አሳዛኝ መሆኑን አቶ ምትኩ አንስተዋል።

ቡድኑ ርሃብን እንደ ጦርነት መሳሪያ መጠቀሙንና ለዚህም ደግሞ አስፈላጊው መረጃ ማቅረብ ቢቻልም እነዚህ አካላት ሊያወግዙት አለመቻላቸውን ነው ያስረዱት።

ያም ሆኖ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ ስራውን ለማሳለጥ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የሰብዓዊ ድጋፉን ይበልጥ ለማጠናከር ከተመድ ኤጀንሲዎች ጋር ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እውቅና መስጠት እንደሚገባና በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ለማውገዝ ተስማምተናል ብለዋል።   

በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ከሥምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ የተመድ ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ በበኩላቸው የተለያዩ የረድኤት ተቋማት የሰብዓዊ ድጋፋቸውን እያሳደጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሁንና በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ስፋት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በቅርቡ በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘውን የምግብ ማከማቻ መጋዘን መዝረፉን ገልጸው የተዘረፈውም የምግብ መጠን እየተጠና መሆኑን ተናግረዋል።

የቡድኑ ታጣቂዎች በሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች ላይ መሳሪያ በመደገን የማስፈራራት ተግባር መፈጸማቸውን ጠቅሰው ይህም ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ነው የገለጹት።   

ድርጊቱ በሦስቱም ክልሎች ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስተጓጉል በመሆኑ እንዲህ አይነት ድርጊት የፈጸሙ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።    

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም