ባንኩ የሆቴል ኢንዱስትሪውን ለማዘመን የሚያግዝ አዲስ ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ

461

ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሆቴል ኢንዱስትሪውን ለማዘመን የሚያግዝ አዲስ ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ።

ቴክኖሎጂው ከኤግልላይን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ቴክኖሎጂው ሶስት ተግባራትን በአንድ ጊዜ ለማከናወን የሚረዳ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂው በዋናነት የግል ሆቴል አገልግሎት የባንኮች እንዲሁም ለተቋማት የሆቴል አገልግሎት ጨረታን በኦን ላይን ለመያዝና ክፍያን ለመፈጸም የሚያገለግል የሞባይል መተግበሪያ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም ወደ አገር ቤት ለመምጣት ያሰቡ ዳያስፖራዎች መሠረታዊ ነገሮችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ይህ መተግበሪያ የአገሪቱን የሆቴል ኢንዱስትሪ በማዘመን እና በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

በስነ-ስርአቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች አስጎብኚ ድርጅቶችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

-አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።