ግጭትን ቀድሞ ለማወቅና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አዲስ የአሰራር ስርዓት ሊዘረጋ ነው

110

ቢሾፍቱ ህዳር 30/2014(ኢዜአ)..የሰላም ሚንስቴር ግጭትን ቀድሞ ለማወቅና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አዲስ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ሚንስቴሩ በአዲሱ የአሰራር ሥርዓት አተገባበር ዙሪያ ከክልሎች የሰላምና ፀጥታ ቢሮዎች ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ እየመከረ ነው።

በሰላም ሚንስቴር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሔ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ምግባሩ አያሌው በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ምክክሩ ያስፈለገው ዘመናዊ የግጭት አስተዳደር ሥርዓት አተገባበርና ፅንሰ ሃሳቡ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ነው።

በተለይም በቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ "ስራዎችን ስንሰራ የነበርነው በተለምዶና ዘመናዊነትን ባልተከተለ ሁኔታ ነው" ብለዋል።

አዲሱ አሰራር መንግሥት የህዝብና የሀገር ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠብቅ የሚያስችል  መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር የግጭት አመላካች ሁኔታዎችና ክስተቶችን ቀድሞ ለማወቅና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቁልፍ ሚና ያለው ነውም ብለዋል።

በዚህም በማህበረሰብ ውስጥ ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ፍላጎቶች፣ አስተሳሰቦችና ተግባራትን በአግባቡ ለመያዝና በወቅቱ ምላሽ ለመስጠት ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል።

በዚህም ዘላቂ የሁኔታ መከታተያና የመረጃ አያያዝ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ይሰራል ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፤ አሰራሩ የሌሎች ሀገራት የግጭት መከላከልና አፈታት ዘዴዎችን እንደ ተሞክሮ ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ቀድሞ ለመፍታትና የሀገር ሰላምና ልማት ለማፋጠን ወሳኝ ድርሻ አለው ብለዋል።

በሚኒስትሩ የግጭት አፈታትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ይትባረክ ተስፋዬ በበኩላቸው  አሰራሩን ለማዘመን ከፓክት ኢትዮጵያ ጋር በመተባበርና የውጭ ሀገር ተሞክሮዎችን በማካተት በሶስት ክልሎች ላይ ተግባራዊ እንደሆነም ተናግረዋል።

በተለይም ተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትባቸው ጋምቤላ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ላይ በአምስት ዞኖችና 12  ወረዳዎች መተግበሩን ገልጸዋል።

በዚህም ተግባራዊ በተደረባቸው ወረዳዎች ላይ የግጭት አመላካች ሁኔታዎችን በመለየትና ፈጣን ምላሽ በመስጠቱ ላይም 96 በመቶ ውጤታማ ሆነናል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ቤንሻንጉልጉሙዝና ሶማሌ ክልሎች እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው አሰራሩን በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በተሰናዳው ውይይት ሰፊ ግንዛቤ እንደሚያዝበትም ይታመናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም