በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ከአምስት ወራት በላይ ሰብዓዊ ድጋፍ አጥተው የተቸገሩ ዜጎች አሉ

243

ህዳር 30 ቀን 2014 (ኢዜአ ) አሸባሪው ሕወሓት ወረራ በፈፀመባቸው በሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና ዋግኸምራ ከአምስት ወራት በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አጥተው ሲቸገሩ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ዝምታ መምረጣቸው አሳዛኝ መሆኑን የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

አሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአንዳንድ ዓለም አቀፉ የማኅበረሰብ አካላት አለመወገዙም አስገራሚ ሆኗል ብሏል።

የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ ጋር በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፤ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላም ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል ብለዋል።

መንግሥት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታውን ለማሳለጥ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ገልጸዋል።

በሦስት ኮሪደሮች በመጠቀም ወደ ክልሉ የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ መደረጉን ጠቁመው ከአዲስ አባበ መቀሌ የአየር ትራንስፖርት ተፈቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም አቶ ምትኩ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የፍተሻ ጣቢያዎችን ከሰባት ወደ ሁለት ማውረድ ተችሏል፤ የሠብዓዊ እርዳታ ለሚሰሩ ሰዎች የሚሰጠውን የቪዛ ቆይታ ጊዜ ከአንድ ወር ወደ ሦስት ወር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የጉዞ መረጃ (የይለፍ) ሰነዶች የማዘጋጀትና የኮሙንኬሽን መሳሪያዎች እውቅና የመስጠት ሁኔታዎችን ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚያግዝ ገንዘብም ከአዲስ አባበ ወደ መቀሌ ይዘው እንዲሄዱ መደረጉን ጠቁመው ያም ሆኖ አንዳንድ አካላት የመንግሥትን ጥረት እውቅና ያለመስጠት ችግር ይስተዋልባቸዋል ብለዋል።

በአንጻሩ የሕወሃት ቡድን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን እየጣሰ ዝምታን መርጠዋል፤ ሲያወግዙትም አይታይም በማለት ተናግረዋል።    

ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው ከገቡት 1 ሺህ 317 የጭነት መኪናዎች መካከል 1 ሺህ 10ሩ ወይም 77 በመቶ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች እስካሁን አለመመለሳቸውን ገልጸዋል።

እነዚህም ተሽከርካሪዎች የአሸባሪውን ሕወሃት ቡድን አማራና አፋርን ለመውረር ታጣቂዎችን እያመላለሱ ቢሆንም ቡድኑ በዚህም ድርጊቱ እየተወገዘ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ሰብአዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ጭነታቸውን አራግፈው ለመውጣት ከ3 እስከ 5 ቀናት ብቻ የሚወስድባቸው ቢሆንም በቅርቡ ወደ ክልሉ ምግብና ምግብ ነክ ሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው የገቡት 203 ተሽከርካሪዎች እስካሁን አለመመለሳቸውን ጠቁመዋል።  

አሸባሪው ሕወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈፀመባቸው አከባቢዎች 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች እንደተፈናቀሉና 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።

ቡድኑ በርካታ መሰረተ ልማቶች ማውደሙንና መዝረፉን ጠቁመው በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያም ፈፅሟል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በሦስቱም ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ ከልክሎ ሳለ አጋር አካላት ይህንን ሁሉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አለማውገዛቸውን ጠቁመዋል።

ሕወሓት በወረራ በያዘባቸው በሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ጎንደርና በዋግኸምራ የሚገኙ ሰዎች ከአምስት ወራት በላይ የሰብዓዊ ድጋፍ አጥተው ሲቀመጡ እነዚህ አከላት ዝምታን መምረጣቸውን አክለዋል።

ቡድኑ ርሃብን እንደ ጦርነት መሳሪያ መጠቀሙንና ለዚህም ደግሞ አስፈላጊው መረጃ ማቅረብ ቢቻልም እነዚህ አካላት ሊያወግዙት አለመቻላቸውን ነው ኮሚሽነሩ ያስረዱት።

ያም ሆኖ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማሳለጥ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የሰብዓዊ ድጋፉን ይበልጥ ለማጠናከር ከ.ተ.መ.ድ ኤጀንሲዎች ጋር ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እውቅና መስጠት እንደሚገባና በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ለማውገዝ ከሥምምነት ተደርሷል ብለዋል።   

በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሥምምነት መደረሱን ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ በበኩላቸው የተለያዩ የረድኤት ተቋማት የሰብዓዊ ድጋፋቸውን እያሳደጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሁንና በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ስፋት ያለው መሆኑን ጠቁመው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ጥሪ የቀረቡት።  

በሌላ በኩል አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በቅርቡ በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘውን የምግብ ማከማቻ መጋዘን መዝረፉን ገልጸው የተዘረፈውም የምግብ መጠን እየተጠና መሆኑን ተናግረዋል።

የሕወሓት ታጣቂዎች በሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች ላይ የማስፈራራት ተግባር መፈጸማቸውን ጠቅሰው ይህም ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ነው የገለጹት።   

ድርጊቱ በሦስቱም ክልሎች ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስተጓጉል በመሆኑ እንዲህ አይነት ድርጊት የፈጸሙ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።