በድሬዳዋ የተስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በስኬት ተጠናቋል

234

ድሬዳዋ፤ ህዳር30/2014(ኢዜአ) 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የታለመለትን ግብ በማሳካት ያለምንም ፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን የድሬዳዋ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ።

ድሬዳዋ ያሉትን የኢንቨስትመንት ምቹነትና ሁለንተናዊ ገጽታ፤ ለአለም ያሳወቀችበት ታላቅ በዓል መሆኑንም ተመልክቷል፡፡

የኮሚቴው  የፀጥታ ዘርፍ አስተባባሪ የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ዛሬ እንደገለጹት፤ ዘንድሮ በአስተዳደሩ የተከበረው በዓል ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትን በማጽናት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል፡፡

ከበዓሉ ዋዜማ እስከ በዓሉ ዕለት  ድረስ በድሬዳዋ የሚገኙ  የፌደራልና የድሬዳዋ የፀጥታ አካላት እንዲሁም የተደራጁ ወጣቶች በተቀናጀ መንገድ ያከናወኗቸው ተግባራት ለተገኘው ውጤት ወሳኝ ሚና አበርክቷል ብለዋል፡፡

ኮሚሽነር አለሙ አክለውም የድሬዳዋ ህብረተሰብ ለበዓሉ መሳካትና ለድሬዳዋ ሰላምና ፀጥታ እያበረከቱት ለሚገኘው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፤ ለበዓሉ የመጡ እንግዶች ዛሬ በሰላም ተሸኝተዋል፡፡

16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የድሬዳዋን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል ከተማነት  ለመላው ኢትዮጵያዊያን ዳግም ማረጋገጥ የተቻለበት ዕድል መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ናቸው፡፡

አቶ እስቅያስ፤ ድሬዳዋ የኢትዮጵያ ቀዳሚ የብልጽግና ማረጋገጫ ማዕከል መሆኗን በአጭር ጊዜ ለማስመስከር የሚያስፈልጓትን መሠረታዊ ጉዳዮች በበዓሉ ለተገኙ የፌደራልና የክልሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ማስረዳት መቻሉ በዓሉን ስኬታማ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር አስተናጋጅነት በተከበረው 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል    የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴና  የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ  ሌሎችም የፌደራልና የየክልሉ አመራሮች፣ የሁሉም የኃይማኖት ተቋማት መሪዎች ፣ባህላዊ የማህበረሰቡ መሪዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና  የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮችም ተሳታፊ መሆናቸውን  ከሥፍራው ተዘግቧል።