የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመከላከያ ሰራዊቱ የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አካሄደ

172

ህዳር 30/2014 /ኢዜአ/ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ16ቱ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ ለመከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አካሄዷል፡፡

በመስቀል አደባባይ በተካሄደው በዚሁ መርሃ ግብር በመዲናዋ ከአስራ አንዱም  ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ሴቶችና እናቶች ተሳትፈዋል፡፡

በሴቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ፅጌ ታደለ የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ  የሚከበረውን የ16ቱ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ቀኑን በማስመልከት 200 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታሰቡን ገልጸው፤ በዚህም በርካታ ሴቶችና እናቶች በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሴቶችና እናቶች ለመከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት የሚገልጹበት መርሃ-ግብር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ስዩም በበኩላቸው ከደም ልገሳው ጎን ለጎን  ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን የስንቅ ማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ  ነዋሪዋ ወይዘሮ ዓይናለም ግዛው በተለያዩ ጊዜያት ደም በመለገስ ለሰራዊቱ ያላቸውን ደጀንነት መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ የክፍለ ከተማው ነዋሪ ወጣት ሀና ሀጫሉ ኀብረተሰቡ ደም በመለገስ በስፋት እንዲሳተፍ ጠይቃለች፡፡