ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አኩሪ የጀግንነት ተጋድሎ ፈጽመዋል

61

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 30/2014 --ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሠራዊቱን በአውደ ግንባር በመምራት የቀደምት የኢትዮጵያን መሪዎች ታሪክ መድገማቸውን የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ገለፁ።


የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ጠላቶች ክብሯንና ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር ሲሞክሩ ዛሬ የመጀመሪያቸው አይደለም።

ጠላቶች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በኢትዮጵያ ላይ ቢዘምቱም በየዘመናቱ የነበሩ መሪዎቿ ከፊት በመሆን ጦራቸውን በመምራት ነፃነቷን አስጠብቀው ቆይተዋል።

ዓፄ ዮሐንስ 4ኛ ግብፅ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ፣ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ሶማሌያ ኢትዮጵያን ስትወር ህዝባቸውንና ሠራዊታቸውን በማስተባበር ጠላትን ድል በመንሳት የተከበረች ሀገር ማስረከባቸውን አንስተዋል።

"የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠላት የእናት ጡት ነካሽ ከመሆን ባለፈ በውጭ ጠላቶች እየተጋለበ ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሰለፉ ከቀደሙት ለየት ያደርገዋል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የእዚህን ባንዳና ተላላኪ ሀገር የማፍረስ ሴራና ህልም በማምከን የቀደምት የኢትዮጵያን መሪዎች ታሪክ መድገማቸውን ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ እንዳሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የጀግኖች አባቶችን የሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ያለማስደፈር ወኔ በማስቀጠል ለቀጣይ ትውልድ ምሳሌ የሚሆን አኩሪ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር የ"ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት"ን በአውደ ግንባር መምራታቸው የአሸባሪውን ህወሓት  ሀገር የማፍረስ  ህልም ማምከኑን ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ ህዝብ መሪውን አክባሪና የመሪውን መልዕክት የሚሰማ ነው" ያሉት አቶ ዳኝነት፣ ህዝቡ የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ዛሬም ከአራቱም አቅጣጫ በመትመም የአባቶቹን ታሪክ እየደገመ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በቀጣይም ለህዝብና ለሃገር ስጋት እንዳይሆን ወጣቱ መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀልና በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን እንዲያጠናክርም ሊቀመንበሩ አቶ ዳኝነት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም