በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገው ማሻሻያ በዓለም አቀፍ ገበያ ካለው የነዳጅ ዋጋ አንጻር አነስተኛ ነው

168

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገው ማሻሻያ በዓለም አቀፍ ገበያ ካለው የነዳጅ ዋጋ አንጻር አነስተኛ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያውን እንደምክንያት በመውሰድ በሸቀጦች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያስታወቀው፡፡

ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ ማስፈለጉን ገልጿል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አህመድ ቱሳ በዚሁ ወቅት መንግሥት እስካሁን በዓለም ላይ እየጨመረ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ንረት ለማረጋጋት ያለውን ልዩነት ተሸክሞ ድጎማ እያደረገ መቆየቱን ተናግረዋል።

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የተደረገው ከስምንት ወር በኃላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር በዓለም አቀፍ ገበያ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 42 ዶላር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ አንድ በርሜል ነዳጅ 85 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህም የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ጉድለት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ያለው  የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነጻጻር በእጥፍ ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ ያለውን የነዳጅ ሽያጭ ለኮንትሮባንድ ንግድ እንዳጋለጠው ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም የዓለም አቀፍ ዋጋን ታሳቢ ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ሲሸፈን የነበረውን የነዳጅ ድጎማ ላይ ኀብረተሰቡ 25 በመቶውን እንዲጋራ የሚያደርግ ጭማሪ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የዓለም የነዳጅ ዋጋ መውጣትና መውረድን ተከትሎ በአገሪቱ እንቅስቃሴ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል በገንዘብ ሚኒስቴር የሚተዳደር የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ መቋቋሙንም ገልጸዋል፡፡

በዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አማካኝነትም በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር በጨመረው ልክ በቀጥታ ወደ ህብረተሰቡ ማስተላለፍ ሳያስፈልግ ልዩነቱ ወደ ማረጋጊያ ፈንድ እንዲተላለፍ ይደረጋል ነው የተባለው።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያውን እንደምክንያት በመውሰድ በሸቀጦች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ለዚሁ ስራ የሚሆን ግብረ ሃይል ማቋቋሙንም ነው የተናገሩት፡፡

በነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ መሠረት ቤንዚን ባለፈው ወር ሲሸጥበት ከነበረው ዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሊትር 31 ብር ከ74 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

እንዲሁም ነጭ ናፍጣ 28 ብር ከ93 ሳንቲም፣ ነጭ ጋዝ 28 ብር ከ93 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 23 ብር ከ73 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 23 ብር ከ 29 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 58 ብር ከ77 ሳንቲም እንደሚሸጥ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።