የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

188

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30/2014(ኢዜአ)  የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊትና አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

የበላይነህ ክንዴ (BKG) ግሩፕ መስራችና ባለቤት ሌሎች ባለሃብቶችን በማስተባበርና ግንባር ድረስ በመሄድ ለሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል።

የደርጅቱ ሰራተኞች ደግሞ በራሳቸው ተነሳሽነት በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው ሰራዊት እና ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን የድርጅቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው ገልጸዋል።

በዚህም የደርጅቱ ሰራተኞች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በተጨማሪም የደም ልገሳ አድርገዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በመገኘት ድጋፉን ለተፈናቃይ ወገኖች የሚያደርሱ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የአፋር ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚና በአዲስ አበባ ለተቋቋመው የአፋር ክልል ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ ኑረዲን ሰዲቅ፤ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ሰራተኞች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ የተቸገሩና የተፈናቀሉ ዜጎችን በመርዳት ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።