በውጭ አገራት ሆነው የአገርን ሉዓላዊነት የሚገዳደር የሕግ ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው

84

ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) በውጭ አገራት ሆነው የአገርን ሉዓላዊነት የሚገዳደር የሕግ ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰሩ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው በውጭ አገራት የሚኖሩ የሕግ ባለሙያዎች ገለጹ።

በሙያቸው ኢትዮጵያን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይበጀኛል ያለውን መርጦ አዲስ መንግስት መመስረቱ ይታወቃል።

በሕዝብ ድምጽ ወደ ስልጣን የመጣ መንግስትን የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ፍላጎት በሚጋፋ መልኩ ለመገልበጥ ማሴር ደግሞ በዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ተጠያቂ የሚያደርግ ከባድ ወንጀል መሆኑን በውጭ አገራት የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በተለይም የውጭ አገር ዜጎች ሆነው የሌላ አገር መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ መዶለት በሚኖሩበት አገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው አመልክተዋል።

በመሆኑም በውጭ አገራት ሆነው በመሰል ወንጀል ላይ የሚሳተፉትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ነው ባለሙያዎቹ የተናገሩት፡፡

በአሜሪካ የሚገኙ አራት የሲቪክ ማኅበራት በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ባደረጉት የበይነ መረብ ስብሰባ የተሳተፉ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እንዲደረግ ለአሜሪካ የፍትህና የደህንነት ተቋማት በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በስብሰባው ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች በአሜሪካ ሕግ መሰረት መንግስት በመገልበጥ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ማቀድ፣ሴራ በማሴርና ሕገወጥ ቡድን መርዳትና መደገፍ የሚሉ የሕግ ማዕቀፎችን መጣሳቸውን አመልክተዋል።

ብሌን ማሞ የሕግና የዓለም አቀፍ ጸጥታ ጉዳዮች ባለሙያ መኖርያቸው  እንግሊዝ ለንደን ነው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደ ስልጣን የመጣን መንግስት አይደለም አምባገነንም መንግስት የዛ አገር አገር ዜግነት የሌላቸው መፈንቅለ መንግስት የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው።  

አቶ ደረጀ ደምሴ ጠበቃ ከአሜሪካ ቦስተን  ሕግ የሚጻረር ግሩፕ ለመርዳት መሞከር  ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በአንድ አገር ውስጥ መንግስት የመገልበጥ ሴራ ማካሄድ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፋ ከመሆኑም ባሻገር በፖለቲካ፣በኢኮኖሚና ደህንነት መስኮች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ቀላል ባለመሆኑ የሕግ ተጠያቂነቱን ደረጃ ከፍ እንደሚል ነው የሕግ ባለሙያዎቹ የገለጹት።

በዋሺንግተን ዲሲ የተደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን አሜሪካ እቆምለታለሁ የምትለውን የዴሞክራሲ መርህ የሚጻረር ነው ብለዋል።  

በውይይቱ ላይ የተሳተፉትን ግለሰቦች ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ሌሎች አካላት እንደዚህ አይነት ድርጊቶች በወንጀል እንደሚያስጠይቃቸውና ከተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይችሉ መልዕከት እንደሚያስተላለፍ አመልክተዋል።

በበይነ መረብ ስብሰባ በማድረግ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ሲያሴሩ ነበሩ የተባሉ ግለሰቦች ዙሪያ የቀረበው አቤቱታ በተመለከተ የቅርብ የሕግ ክትትል እንደሚደርግ ጠቁመዋል።

የሕግ ባለሙያዎቹ በተቻላቸው አቅም በሙያቸውና በእውቀታቸው የኢትዮጵያን ጠቅም ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም