በአሸባሪው ህወሃት የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

61

ህዳር 30/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ያደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት ከመንግስት በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግስት ጥሪ አቀረበ።

አሸባሪ ቡድኑ በፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ እና የሀብት ውድመት ተጠያቂ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውንም መንግስት አስታውቋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ እንዳሉት  የ'ዘመቻ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት' የማጥቃት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያዊያንን ሕብረት ያሳዬ፣ የወታደራዊ አመራር ጥበብ የተሞላበትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አስደናቂ ድል ነበር።

በዚህም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የደረሰበት ወራሪው ቡድን ተበታትኖ በመሸሽ ላይ ሲሆን "አዲስ አበባ እየገባሁ ነው" በሚል የትግራይ ህዝብና  የዓለምን ማህበረሰብ ሲያደናብር ቢቆይም ቅዥቱ ግን ከንቱ ቀርቷል ብለዋል።

በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች መካከል አፋር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻልበት ደረጀ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ አስተዳድር ልዩ ዞን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በሰሜንና ደቡብ ወሎ ስትራቴጂክ ስፍራዎችን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ከወራሪው ነፃ ወጥተዋል ብለዋል።

ይህም በትግራይ ክልል ከሚኖሩ ወላጆች "ልጆቻችንን የት አደረሳችሁ፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እጣልታችሁን ዕጣ ፈንታችን ምንድነው" የሚል ተቃውሞ ተቀስቅሶበታል ነው ያሉት።

በዚህም ቡድኑ የመጨረሻ መቃብር እየቀረበ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዘመቻውን ሲመሩ የነበሩ ጠቅላይ ማኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለጊዜያዊነት ወደ ቢሮ መመለሳቸውን አስታውሰው፤ ወራሪውን  ሃይል የማጥቃት ዘመቻው ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ነጻ የወጡ አካባቢዎችም የመንግስት አስተዳደር እየተደራጀና የመብራትና የቴሌኮም መሰረተ ልማት አገልግሎት ዝርጋታም እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች ህፃናትና አዛውንት ሴቶችን ጨምሮ አስገድዶ መድፈር፤ ከፍተኛ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸም፣ በንብረት ወድመትና ዘረፋ መፈፀሙን ገልፀዋል።

በወንጀሉ የተሳተፉ አካላት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን የሚያከናውን አደረጃጀት ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በደረሰባቸው ስፍራዎች ሁሉ ያደረሰውን ውድመት በመንግሥት ጥረት ብቻ መልሶ መገንባት የሚቻል አለመሆኑንና የመላው ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን የትብብር እጆች የሚሻ እንደሆነም ጠይቀዋል።

በተጨማሪ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትወልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አንዳንድ ምዕራባዊን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃገብነትና ጫና በመቃወም ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።

"#በቃ" የተሰኘውን ንቅናቄ የአፍሪካዊያን በስፋት እየተቀላቀሉት መሆኑንም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ቢሯቸው ከተመለሱ በኋላ ከተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሃመት እና ከተለያዩ የጎረቤት አገራት መሪዎች ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ የስልክ ውይይት ስለማድረጋቸው አንስተዋል።

ከውይይታቸው ነጥቦች መካከልም "ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ ያላት አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያስፈልጋታል" የሚለው ይገኝበታል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በአሸባሪው ሸኔ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ ባለፉት ሳምንታት ከወለጋ እስከ ጉጂ በርካታ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ተደምስሰዋል ብለዋል።

አሸባሪው ሸኔ በየጫካው እየተሹለከለከ ንፁሀንን በማንነታቸው ለይቶ የሚጨፈጭፍና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች የሚገድል የመንደር ሽፍታ መሆኑንም ገልፀዋል።

ኀብረተሰብም በየአካባቢው የተሰገሰጉ የአሸባሪው ሸኔ አባላትን የማጋለጥና አካባቢውን የመጠበቅ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በሳምንቱ ኀብረተሰቡ በደጀንነትና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚያደርገውን እርዳታ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው፤ በቀጣይም ደጀንነቱን እና ተጎጂዎችን የማቋቋም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይም ኃይማኖታዊ በዓላት እየቀረቡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰርጎ ገቦች ጥፋት እንዳይደርሱ ኀብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበትም አስገንዝዋል፡፡

በኢኮኖሚ ግንባር የተጀመረው የምርት ስብሰባ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀው፤ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ሰብል በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች የተጠናከረ የመስኖ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚም የባለድርሻ አካላት የተጠናከረ ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ወደ አገር ቤት የሚገቡ የዲያስፖራ አባላትም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁሉን አቀፍ ዕድገት እውን ለማድረግ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም