የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሐፈት ቤት ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ገለፁ

116

ህዳር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሐፈት ቤት ሠራተኞችና አመራሮች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ሠራተኞቹናና አመራሮቹ ዛሬ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

ከዚህ ቀደም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰጡት የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች የስንቅና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግም ግንባር ቀደም መሆናቸውን ገልፀዋል።

አሁንም ሕይወቱን ሰውቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያስከበረ ለሚገኘው ሠራዊት የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ የአገልግሎቶችና መልካም አስተዳደር ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሀይ ጳውሎስ ሠራተኞቹና አመራሩ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች ወይዘሮ ጽጌ ብርሃኑ እና ወይዘሪት ታደሉ ኡማ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት አቻ የማይገኝለት ዋጋ እየከፈለ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም በአቅሙ ልክ በሞራል ጭምር አለንላችሁ በማለት ለሠራዊቱ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች ከደም ልገሳ በተጨማሪ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ዓለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ የጸረ ፆታዊ ጥቃት እና የዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀናትን በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም