የአገራችን ሕልውና በአስተማማኝ ሁኔታ እስከሚከበር ድጋፋችንን እንቀጥላለን

339

ህዳር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕልውና በአስተማማኝ ሁኔታ እስከሚከበር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የለሚ ኩራ ክፍለከተማ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የለገዳዲ ለገጣፎ አስተዳደር ነሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ለመከላከያ ሠራዊት 100 ኩንታል ስንቅ አዘጋጅተዋል፡፡

የሁለቱ አካባቢዎች ነዋሪዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ጣፎ አደባባይ በመሰባሰብ ያዘጋጁት ዳቦቆሎ፣ ቆሎና በሶ በራሳቸው ተነሳሽነት የተሰባሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

የለሚኩራ ክፍለከተማ ነዋሪው ምክትል አስር አለቃ ወንደሰን ኪሮስ የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ አገር የማፍረስን አደጋ ለመመከትና ከሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት በሥንቅ ዝግጅቱ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የለገጣፎ ለገዳዲ ነዋሪዋ ወይዘሮ ራሄል ደፈርሻ በበኩላቸው የአሸባሪዎቹ አገር የማፍረስ ጥረት በጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ድባቅ እየተመታ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ይህን መሰል ዝግጅታቸውን የኢትዮጵያ ሕልውና እስከሚከበር ድረስ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

የለሚ ኩራ ክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ መላኬ አለማየሁ ክፍለከተማው ከአጎራባቹ ለገጣፎ ለገዳዲ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስራዎችን ሲከውን መቆየቱንና የስንቅ ዝግጅቱን የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ክፍለከተማው ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሠራዊት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ የሕልውና ዘመቻው እስከሚጠናቀቅ ድጋፉ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የለገዳዲ ለገጣፎ አስተዳደር ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስገን ከአጎራባች አስተዳደሮች ጋር በመቀናጀት በሠላም ማስከበርና በተለያዩ የልማት ስራዎች እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን ለማጥፋት የሚደረገውን ዘመቻ እየደረጉ ለሚገኙ ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።