ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ሲጎለብት አሸናፊነታችንም እሙን ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

211

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ)ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ሲጎለብት አሸናፊነታችንም እሙን የመሆኑ ጉዳይ በታሪካችን የነበረ ብቻ ሳይሆን ዛሬም እተመሰከረ ያለ ሀቅ ሆኗል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን አንኳን ለ16ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሰላም አደረሳቸሁ መልዕክት አስተላልፏል።የመግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።-

የዘንድሮዉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞኪራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመቻቻልና የፍቅር ተምሳሌት በሆነችዉ በድሬ ዳዋ ከተማ ህዳር 29/2014 ዓ.ም ተከብሯል፡፡

ዕለቱ “ወንድማማችነት ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን ዕለቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተብሎ መከበር የጀመረዉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት የፀደቀበት ቀን ምክንያት በማድረግ ነው ፡፡

ከለዉጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ዕለቱ በተለያዩ ሕዝባዊ ክንዋኔዎች ሲከበር የቆየ ቢሆንም በዋናነት ልዩነቶችን በማጉላት ላይ ያተኮረና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የሚቆጠር ሚና አልተጫወተም።

በመሆኑም የለዉጡ ጉዞ ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት የሚረጋገጠዉ ዕለቱን አስቦ ከመዋል ባሻገር በሕገ-መንግስቱ ዉስጥ የተደነገጉ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ድንጋጌዎችና መርሆች እንዲከበሩ በማድረግ ጭምር መሆኑ ታምኖበት ትርጉም ያላቸው የለዉጥ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡የግልና የቡድን መብት ይበልጥ እንዲጠበቁ ተደርጓል፡፡

እዉነተኛ ህብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት እንዲገነባ ተሰርቷል። ልዩነታችን የስጋትና የመከፋፈል መንስኤ ሳይሆን የጥንካሬያችን ምንጭና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ማጌጫ ሆኖ እንዲያገለግል መሰረት በመጣል ላይ እንገኛለን፡፡

ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረዉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲከበርም ዕለቱ የአንድ ቀን መታሰቢያ ከመሆን አልፎ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ይበልጥ በሚረጋገጡበትና በልዩነት ዉስጥ የተፈጠረ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እሴቶችን በሚያጎለብቱ ተግባራት ተከብሯል፡፡

የዘንድሮዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበርን ከወትሮዉ ልዩ የሚያደረገዉ ለ27 ዓመታት በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስም እየማለ ነገር ግን በተግባር አንዱን ብሔር ከሌላዉ ብሔር ጋር እያጋጨ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትቀጥል ሲሰራ የነበረዉና በጦርነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪዉ የህወሃት ቡድን በብሔሮች አንድነት ወገቡ በተሰበረበት ማግስት መሆኑ ነዉ፡፡

አሸባሪዉ ቡድን ኢትዮጵያን ይበታትናል ብሎ የቀበረውን ፈንጂ በመተማመን ጦርነት ቢከፍትም አሸባሪዉ ቡድን ባልጠበቀው ሁኔታ የፈረሰ የመሰለዉ ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ይበልጥ ተጠናክሮ ወጥቷል፡፡

ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ሲጎለብት አሸናፊነታችንም እሙን የመሆኑ ጉዳይ በታሪካችን የነበረ ብቻ ሳይሆን ዛሬም እተመሰከረ ያለ ሀቅ ሆኗል። በመሆኑም ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ያጋጠሙንን ፈተናዎች እንሻገራለን፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት