የአሶሳ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለአገራቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታወቁ

298

አሶሳ፣ ህዳር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሶሳ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለአገራቸው አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን ሁሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታወቁ።

በሰብል ስብሰባ ዘመቻ የተሳተፉት ተማሪዎቹ የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ደም ለግሰዋል።

ተማሪዎች ለሰብል ስብሰባ ዘመቻ እንዲሰማሩ ለአንድ ሳምንት ትምህርት እንዲዘጋ የተላለፈውን ውሳኔ በማዛባት የተሳሳተ ዘገባ የሰሩትን የውጭ ሚዲያዎች አውግዘዋል።

ዘገባው ሚዲያዎቹ ምን ዓይነት እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የደረሰ ሰብል እንዲሰበስቡ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በቤኒሻንጉልጉሙዝ ክልል የሚገኙ ተማሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጥሪው ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻው የዜግነት ግዴታቸውን እዲወጡ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት ውድ ህይወታቸውን ጭምር እየከፈሉ በሰላም እንድንማር አድርገዋል” ያሉት ተማሪዎቹ፤ ለሠራዊቱ ደም በመለግስና በስንቅ ዝግጅት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

አንዳንድ ምዕራባዊያንና ሚዲያዎቻቸው ለአሸባሪው ህወሓት ወግነው በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ የሀሰት መረጃ ማሰራጨታቸው የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በቁጭት እንዲነሳሱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

በሰላም መማርም ሆነ ሁሉን ነገር ማድረግ የሚቻለው ኢትዮጵያ ስትኖር መሆኑን ገልጸው፤ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

የአሶሳ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኢብሳ ገቢሳ ተማሪዎች ትምህርት ሚኒስቴር ላቀረበው ጥሪ በአገራዊ ስሜት ምላሽ እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች ከስንቅ ዝግጅት እና ደም ልገሳ በተጨማሪ በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እያሰባሰቡ መሆኑን ጠቁመው፣ ቤተሰቦቻቸውም የበኩላቸውን ደጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል

ርዕሰ መምህሩ እንዳሉት በዘመቻው የትምህርት ቤቱ መምህራን በገንዘብና እና በጉልበት አስተዋጾ እያደረጉ ይገኛሉ።

የአገርን ሰላም ማስጠበቅ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው” ያሉት ርዕሰ መምህሩ፤ “መከላከያው ጠላትን በግንባር ሲፋለም ሌሎች አካባቢን ከመጠበቅ ጀምሮ በተለያዩ ድጋፎች ማገዝ ይኖርብናል” ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።