ምሁራን የፈጠርነውን ሀገራዊ አንድነት ወደ ሀገር ግንባታ ልንለውጥ ይገባል አሉ

94

ዲላ፤ ህዳር 29/2014 (ኢዜአ ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጫናዎችን ለመቋቋም የተፈጠረውን ሀገራዊ አንድነት ወደ ሀገር ግንባታ መለወጥ እንደሚገባ ገለጹ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ 16ኛውን የኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን በዓልን  በፓናል ውይይት፣ በደም ልገሳና በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የብሔር ብሔረሰቦች መብት በህገ መንግሥቱ ቢቀመጥም አሸባሪው ህውሓት የግል ፍላጎቱ ማስፈጸሚያ መሳሪያ አድርጎ ሲጠቀምበት እንደቆየ ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ የተከናወኑ የአዲስ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥታት ምስረታና ምርጫ የታፈኑ የህዝብ ድምጾች የመደመጥ ዕድል ያስገኙ ናቸው።

ከዚህም ባሻገር ህዝቡ የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ስለመሆኑ ተጨባጭ ማረጋገጫዎች መሆናቸውንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

''የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን  ጫናዎች ለመቋቋም በውስጥም በውጭም ያለን ኢትዮጵያዊያን በጋራ ቆመን ድል እየተጎናጸፍን ባለንበት ወቅት መሆኑ ለዩ ያደርገዋል'' ብለዋል።

ለሀገር በጋራ የመቆም መልካም ጅማሮውን ወደ ሀገር ልማትና ብልጽግና ለመለወጥ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ዳዊት ሃዬሶ እንዳሉት አሸባሪው ህውሓት ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ወደ ጦርነት ማምራቱ ወትሮም ቢሆን ለሀሳብ የበላይነት ቦታ እንደማይሰጥ በተጨባጭ ያሳዬ ነው።

ኢትዮጵያ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክና ድሎች ባለቤት መሆኗን ያስታወሱት ዶክተር ዳዊት፤ አሸባሪው ህውሓት ይህን መዘንጋቱ የሽንፈቱ ጅማሮ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የህልውና ዘመቻው አሸባሪው ህውሓትንና ተላላኪዎቹን ከማሸነፍ ባለፈ በወረቀት ላይ ብቻ የነበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ህገ መንግሥታዊ ዋስትናን ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

አሁን የተፈጠረውን ሀገራዊ አንድነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራዊ  ልማቱን ለማፍጠን መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የዩኒቨርስቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ኃይለማሪያም ማሞ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በህገ መንግሥቱ የፌዲራላዊ ሥርዓት ሀገር ብትሆንም አሸባሪው ህወሓት ላለፉት 27 ዓመታት ሥልጣኑን ሁሉ ወደ ራሱ ሰብስቦ አሃዳዊ አድርጎት እንደነበር አስታውሰዋል።

''ዛሬ ብሔር ብሔረሰቦች በትግላቸው እኩል ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ሲጀምሩ የኢትዮጵያዊያንን    ድምጽ ቀምቶ አሀዳዊያን እያለ የሚጮኹ ዳግም የይስሙላ የፌዲራል ሥርዓት ለመዘርጋት ካለው ፍላጎት'' የተነሳ ነው'' ብለዋል።  

የአሸባሪው ህወሓትን ተግባርና አስተሳሰብ ከማፍረስ ባለፈ እኩል ተጠቃሚነትንና ሀገራዊ ልማትን ለማጎልበት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ መምህራን ተማሪዎችና የአስተዳደር ስራተኞች የተገኙ ሲሆን፤ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳና ለተፈናቀሉ ወገኖች የአይነት ድጋፍ የማሰባሰብ መርሃ ግብሮች ተከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም