የጠላትን ሐሰተኛ መረጃ በማጋለጥ ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው

237

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) የውጭና የአገር ውስጥ አፍራሽ ኃይሎችን ሐሰተኛ መረጃ በማጋለጥ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ ለአገር መከላከያ ሠራዊት 4 ሚሊዮን ብር እና 25 ሰንጋዎችን አበርክቷል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ንጉሴ መሸሻ ድጋፉን ሲያስረክቡ ዋልታ የህወሓት አሸባሪ ቡድንና ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን የሚያወጡትን ሐሰተኛ መረጃ በማጋለጥ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ጥቃት በመመከት ሕይወቱን አስይዞ ፊት ለፊት እየተፋለመ ለሚገኘው መከላከያ ድጋፍ ማድረግ ሠራዊቱን ማጀገን መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በዚህ ሂደት የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ከዛሬው ድጋፍ ባሻገር ቀደም ሲልም ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ሲያሳዩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

ኮርፖሬሽኑ በቀጣይም የሕዝብን ጥቅም በማስጠበቅ ኢትዮጵያ በአሸናፊነቷ እንድትቀጥል በተጠናከረ መልኩ ሥራውን ያከናውናል ብለዋል።

በቀጣይም የህወሓት አሸባሪ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ካስከተለው ጉዳት መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ በጎ አድራጊዎች ጥምረት 1 ሺህ 500 ኪሎ ግራም ቴምር ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስቴር ፋይናንስ ዳይሬክተር ብራጋዴር ጄኔራል ዘላለም ፈተና ሠራዊቱ ድል እየተቀዳጀ መሆኑን ገልጸው፤ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ ድል ሞራል መሆኑን ገልጸዋል።

እየተገኘ ያለው ድል የመላው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው መልዕክት ያስተላለፉት።