ሁለት ተቋማት ለተፈናቃዮችና ለጸጥታ ኃይሎች 21 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

70

ሰመራ ፤ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአፋር ክልል ለተፈናቃዮችና ለፀጥታ ኃይሎች ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ።
ከጠቅላላው ድጋፍ ሚኒስቴሩ 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ሲያበረክት፣ቀሪውን  ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ነው።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ድጋፉን ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ተረክበዋል።

ሚኒስቴሩ ለፀጥታ ኃይሎች 10 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ፣ ሰባት ሰንጋዎችና 800 ደርዘን እሽግ ውሃ መስጠቱ በርክብክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
  እንዲሁም የአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 100ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 600 ፍራሾችና  የምግብ ዘይት በክልሉ አሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለፀጥታ ኃይሎች 10ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ሰንጋዎች፣ ፍየሎች የለገሰ ሲሆን፤ለክልሉ ተፈናቃዮች የሚውል  የዳቦ ዱቄት፣ ብርድ ልብሶችና  ብስኩት አበርክቷል።

አቶ አወል፤ ተቋማቱ ያደረጉት ድጋፉ የፀጥታ ኃይሎች ሀገርን መታደግ ተልዕኳቸውን በብቃት የሚወጡበት ጠንካራ ሕዝባዊ ደጀን እንዳላቸው የሚያሳይና የተፈናቃዮችን ችግር የሚያቃልል ነው ብለዋል።

ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍም ምስጋና  አቅርበዋል።

ወይዘሮ ዳግማዊ በበኩላቸው ፤ ድጋፉን የአፋር ክልል ሕዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን አሸባሪው የህወሃት ቡድንን  በመዋጋት የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር ያደረገው ተጋድሎ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ፤ ተቋሙ በቀጣይም የከተማዋን ሃይማኖት ተቋማት በማስተባበር ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያሰባስብ አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን አሸባውን ህወሓት በመመከት ላሳዩት የላቀ አመራር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የላከው ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል።









የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም