የሕጻናት መቀንጨርን በመጪዎቹ 10 ዓመታት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እየተሰራ ነው

94

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) በመጪዎቹ አስር ዓመታት ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚታየውን መቀንጨር በሽታ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እየሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
አገር አቀፍ የስርዓተ ምግብ ምርምር አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ያልተመጣጠነ እና ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ወቅቱን ያገናዘበ ሳይንሳዊ ምርምር በማካሄድ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹትም ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨር በሽታ በመጪዎቹ 10 ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ለመቀነስ እየተሰራ ነው፡፡

በተጨማሪም ዕድሜያቸው ከሁለት እስከ አምስት ዓመት የሆኑ ሕጻናትን የመቀንጨር ችግር እስከ 13 በመቶ ለመቀነስ ታቅዷል ብለዋል።

ስርዓተ ምግብ አወሳሰድ የሚታዩ ፈተናዎችን ለመቀነስ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንና አሁንም የምግብ እጥረትና የጤናማ አመጋገብ  ጉዳዮች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በወቅታዊ ሁኔታዎች ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ከገጠማቸው ችግርና ከሌሎችም   ነባራዊ ሁኔታዎች  ጋር ተያይዞ  ጤናማ  አመጋገብ ከፍተኛ  ትኩረት የሚሻ መሆኑን አጽንኦተ ሰጥተዋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕጻናት የጤና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው የመቀንጨርን ችግር በየዓመቱ  እስከ 4 ነጥብ 9 በመቶ  ለመቀነስ  ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

በተለያየ ዘርፍ የሚሰሩ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ውሳኔ ሰጪዎችና የሥርዓተ ምግብ አማካሪዎች የተሳተፉበት አገር አቀፉ የሥርዓተ ምግብ ምርምር አውደ ጥናት ለሦስት ቀናት ይቆያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም