በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ለስነ-ልቦና ችግር ለተዳረጉ ዜጎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው

75

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) በሽብር ቡድኑ ህወሓት ወራሪዎች የተለያዩ ጥቃቶች የደረሱባቸውን ዜጎች የስነ-ልቦና ችግር ማቃለል የሚያስችል አገልግሎት በአካባቢያቸው እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሽብር ቡድኑ ወራሪ በአማራና በአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በፈጸመው ጥቃት የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረትም ወድሟል።

አሸባሪው ወራሪ ዜጎችን በጅምላ ጨፍጭፏል፣ ሕፃናትና እናቶች ሳይቀሩ ደፍሯል፣ ሌሎች ኢ-ሠብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል፤ በዚህ እኩይ ድርጊቱም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ አለሚቱ ኡሙድ፤ ሚኒስቴሩ እስካሁን በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነት እና 116 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት እንከብካቤ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ዕቅዱን ወደ ክልሎች አውርዶ ለመተግበርም ከሴት አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

በሽብር ቡድኑ ወራሪዎች የመደፈርና የተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ ሆነው የስነ-ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አምስት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሚኒስቴሩ ባለሙያዎች ወደተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው የተፈፀሙ ጥቃቶችን የመለየት ሥራ እያከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አያይዘውም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከሠራዊቱ ጋር በግንባር መሰለፋቸው በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ እንዳስቻለ አንስተዋል።

ኅብረተሰቡም በሁሉም አውደ-ግንባር በመረባረብ አገሪቷን ወደ ቀደመ ሠላሟ ለመመለስ ጥረት ማድረግ አለበትም ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነትና በወገን ጦር ትግል በርካታ ድሎች እየተመዘገቡና በአሸባሪው ቡድን በወረራ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችም ነፃ እየወጡ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም