"በቃ" የተቃውሞ ንቅናቄ ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገሩ ጉዳይ በአንድነት እንዲቆም አስችሏል

68

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለውን ያልተገባ ጫና በመቃወም እየተካሄደ ያለው የ"በቃ" ንቅናቄ ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገሩ ጉዳይ ላይ በአንድነት እንዲቆም ያስቻለ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ።
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆች በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ያልተገባ የውጭ ጫና እና ጣልቃ ገብነት በመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።  

በቅርቡ በስፋት እየተደረገ የሚገኘው የ"በቃ" ወይም "#NoMore" የተቃውሞ ንቅናቄ በበርካታ የዓለም ክፍሎች ተካሂዷል፤ እየተካሄደም ይገኛል።

የውጭ ሃይሎችን ያልተገባ ጫና የኮነነ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የደገፈ እንዲሁም አሸባሪው ህውሃት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በንጹሃን ላይ የሚፈፅመውን ግዲያና የንብረት ዘረፋ ያወገዘ ንቅናቄ ነው።

በዚሁ የ"በቃ" ንቅናቄ በርካቶች ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን የገለጹበት መሆኑ ተስተውሏል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እንድሪስ፣ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ የሚያደርጉት ያልተገባ ጫና በንቅናቄው ተወግዟል ብለዋል።

የምዕራባውያኑ ጣልቃ ገብነትና ጫና እንዲቆም እንዲሁም አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት ሀሰተኛ ዘገባ እንዲቆም በንቅናቄው ተጠይቋል።

የ"በቃ" ንቅናቄ ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገሩ ጉዳይ ላይ በአንድነት እንዲቆም ያስቻለ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የ"በቃ" ንቅናቄ በተለይም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የዲፕሎማሲ ጫናውን ለመቋቋም የሚረዳ ከመሆኑም ባሻገር በዓለም ህዝብ ዘንድ ሊኖር የሚችለውን የተሳሳተ አረዳድ የሚያስተካክል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ንቅናቄው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።  

በአሜሪካ እና ሌሎችም አውሮፓ አገራት ላይ ንቅናቄው በስፋት እየተከናወነ ሲሆን በቀጣይ በተለያዩ የአፍሪካ አገራትም ቀጥሎ እንዲካሄድ ለማድረግ ዝግጅቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በውጭ አገራት በአፍሪካውያን የተመሰረቱ የምሁራን ማህበራትና የሲቪክ ማህበረሰቦችም ንቅናቄውን እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

በ "በቃ" ወይም "#NoMore" ንቅናቄ እስካሁን በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ኤሲያ አህጉር እንዲሁም በኦሽኒያ መካሄዱን ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም