አሸባሪው የህወሃት ቡድን በደሴና ኮምቦልቻ በንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያና ድብደባ ከመፈጸም በተጨማሪ በርካታ ግፎችን ሰርቷል

89

ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል በደሴና ኮምቦልቻ ከተማ የመንግስትን እና የግለሰቦችን ንብረት ከመዝረፍና ከማውደም ባለፈ በንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያና ድብደባ በመፈጸም በርካታ ግፎችን ማድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመራው የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣ ከደሴና ኮምቦልቻ በተጨማሪ በምሥራቅ ግንባር ባቲን፣ ቀርሳን፣ ገርባንና ደጋንን ነጻ ያወጣ ሲሆን በሐርቡ ግንባር ደግሞ ቃሉ ወረዳን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ ይታወቃል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዞ ለጥቂት ቀናት በቆየባቸው ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የመንግስትን እና የግለሰቦችን ንብረት ከመዝረፍና ከማውደም ባለፈ በንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያና  ድብደባ በመፈጸም በርካታ ግፎችን ማድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች  በከተማዋ ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት  ፈጽመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ የከተማዋን ወጣቶች በተለያየ ስም በመፈረጅ ድብደባና ግድያ እንደፈጸሙም ገልጸዋል፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ ያሉ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማውደማቸውንና ትልልቅ ፋብሪካዎችን ሳይቀር ነቅለው መውሰዳቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት መዝረፋቸውንና መውሰድ ያልቻሉትን ደግሞ ማውደማቸውን ገልጸዋል፡፡

ንጹሃንን በአደባባይ መግደል፤ ሌሊት በር እያንኳኩ ዘረፋ መፈጸም የሰርክ ተግባራቸው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የአሸባሪው ህወሃት አባላት ወደ ከተማዋ ከገቡበት እለት አንስቶ በግድያ፣ አስገድዶ መድፈር ፣ዘረፋና ድብደባ ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የወራሪው ቡድን አባላት በቡድን በመሆን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ሴቶችን መድፈራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በመንገድ የሚንቀሳቀሰውን ነዋሪ አስቁመው በመበርበር ከሞባይል ስልክ ጀምሮ ያገኙትን ንብረት መዝረፍ፣ ህብረተሰቡን ማሸማቀቅ፣ ጨለማን ተገን አድርገው ተቋማትን መዝረፋና ግድያ መፈጸም መለያቸው ነበር ብለዋል፡፡

እናቶች የጋገሩትን እንጀራ ከልጆቻቸው አፍ ላይ በመቀማት ይወስዱ እንደነበር በመግለጽ "የደበቃችሁት ንብረት አለ አውጡ" በማለት ህብረተሰቡን በድብደባ ሲያሰቃዩ መቆየታቸውን ነው የገለጹት፡፡

በተለይም በከተማዋ የሚኖሩ የባለሃብቶችን ስም ዝርዝር በመያዝ ቤት ለቤት እየዞሩ ዘረፋ መፈጸማቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ጁንታው አከርካሪው ተሰብሮ በመፈርጠጥ ላይ መሆኑን ተናግረው በከተማዋ ከጁንታው ጋር በመተባበር ንብረት በዘረፉና ባዘረፉ አካላት ላይ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

የከተማዋ ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢያቸውን እንዲጠብቁም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም