አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በወረራ ይዟቸው በቆየበት አካባቢዎች በህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ፈጽሟል

72

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በወረራ ይዟቸው በቆየበት አካባቢዎች በህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን የአፋር ልማት ማህበር አስታወቀ፡፡

ከተመሰረተ 10 ዓመታትን ያስቆጠረው የአፋር ልማት ማህበር በዋናነት የክልሉን ነዋሪዎች ህይወት ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡

የአፋር ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን ሳዲቅ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ በተለይ በክልሉ ትምህርት ቤቶችን፣የጤና ተቋማትንና ሌሎች መሰረት ልማቶችን ማስገንባቱን ነው ያነሱት፡፡

አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ማህበሩ ያስገነባቸውን ጨምሮ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ማውደሙን ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪ የጤና ተቋማትን ማውደሙንና የመንገድ ፕሮጀክት ቁሳቁሶችን እንደዘረፈ ገልጸዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ያወደማቸውን ሃብቶች መልሶ ለማቋቋም በርካታ ገንዘብ እንደሚጠይቅም ነው ያወሱት፡፡

ማህበሩ በቅርቡ የወደሙ ንብረቶችን የሚመለከት ጥናት እንደሚያከናውን ጠቅሰው፤ በጥናቱ መሰረት መልሶ የማቋቋም ስራው እንደሚጀመር አውስተዋል፡፡

ማህበሩ ያሉትን አቅሞች በሙሉ በመጠቀም ተቋማቱን ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚንቀሳቀስም ጨምሮ ገልጸዋል፡፡

ከማህበሩ አቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለማሟላት እንደሚሰራም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በክልሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም