ከሌሎች ሀገራት ስህተት ምን እንማራለን? – (ክፍል 2)

112

በሄኖክ ታደለ

በምእራባውያን ተጽእኖ የተነሳ ብሩህ የዲሞክራሲና የእድገት ጉዟቸው ሆነ ተብሎ እንዲጨልምባቸው የተደረጉ በርካታ ሀገራት አሉ፡፡ ዲሞክራሲ እና ልማት ለምእራባውያን ብቻ የተፈቀዱ እስኪመስል ድረስ በልዩ ልዩ ሴራ ከድህነት አዙሪት እንዳይወጡ ተደርገው የቀሩ ሀገራትም አሉ፡፡ ይሁንና ምእራባውያን የሌሎች ሀገራትን የተፈጥሮ ሀብት ለመመዝበርም ሆነ አካባቢያዊ ተጽእኗቸውን ለማስፋት እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቅሱት ሰብአዊ መብትን፣ ዲሞክራሲን እና ሌሎች ቅዱስ ምክንያቶችን ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት እትሜ ኢራን ዲሞክራሲ ለመመስረትና ዘመናዊነትን ለማስፋፋት የነበራት ውጥን እንዴት ሆን ተብሎ በምእራባውያን ጣልቃ ገብነት እንደተሰናከለ አሳይቻለሁ፡፡ የኢራናውያን ንቃተ ሕሊና እስኪዳብር ድረስ የሀገሪቱ ነዳጅ ዘይት ሌት ተቀን እንደተመዘበረ ተመልክተናል፡፡ በዛሬው እትማችን ደግሞ የሶሪያን የእርስ በእርስ ጦርነት አጀማመር ትክክለኛ ምክንያት በትነን እናየዋለን፡፡ ከዚያም ሀገራችን ምን ዓይነት ትምህርት መውሰድ እንደሚገባት እንመለከታለን፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህንን ፅሑፍ ካነበቡ በኋላ የሶሪያን ጦርነት አስመልክቶ ከምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን አንድም ቀን እውነቱን ሰምተው እንደማያውቁ ይረዳሉ፡፡

የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን አይንገሩን እንጂ የሶሪያና እና የዩክሬን ጦርነት የአንድ ምእራፍ ሁለት ክፍሎች ናቸው፡፡ ውጥኑ በአጭሩ ሲጠቃለል "የሩሲያን የኢኮኖሚ መሠረት መስበር ፣ የሀገሪቱን ባህር ኃይል በአንድ ጊዜ ከሜዲትራኒያን እና ከጥቁር ባህር አባሮ ተራ ሀገር ማድረግ ነው፡፡" በዚህ ትልቅ ፕሮጀክት ውስጥ ሶሪያና ዩክሬን የመስዋእት በግ ነው የሆኑት፡፡ ሴራው እንዲህ ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር 1991 ታላቋ ሶቪየት ሕብረት በይፋ ተበታተነች፡፡ የሶቪየት ሕብረት አብዛኞቹ ወደቦች ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር በበረዶ ግግር የሚዘጉ ስለነበሩ ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት የሚሰጡት በዩክሬን የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኙት የወደብ ከተሞች ነበሩ፡፡ የዩክሬን ወደቦች ለሜዲትራኒያን ባህርና ለአውሮፓ ገበያ ቅርብ ስለነበሩ 40 በመቶው የሶቪየት ሕብረት ኢንዱስትሪ የከተመው በዚያኔዋ የዩክሬን ክፍለ ሀገር ነበር፡፡

በመሆኑም ከሁሉም የቀድሞ የሶቪየት ግዛቶች ይልቅ የዩክሬን መገንጠል የሩሲያን ኢኮኖሚ እጅጉን አንኮታኮተው፡፡ ይህ ደግሞ ለአሜሪካ ፖለቲከኞች ሰርግና ምላሽ ሆነላቸው፡፡ ለሩሲያ የነበራቸው ንቀትም ለከት አጣ፡፡ አፈር ትቅለላቸው እና የሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው በባራክ ሁሴን ኦባማ የተሸነፉት የአሪዞናው ሴናተር ጆን ማኬን በተደጋጋሚ " ሩሲያ ሀገር መስሎ ለመታየት የምትጥር ነዳጅ ማደያ ናት!" ሲሉ ተደመጡ፡፡ ያው ሀገሪቱ ኢንዱስትሪ የሌላትና እንደታዳጊ ሀገር የተፈጥሮ ሀብት ብቻ የምትቸረችር ነች ለማለት! እኚሁ ሴናተር በሌላ ጊዜም "በአሁኑ ጊዜ ሩሲያ የምታስፈራ ሀገር አይደለችም -ኒውክሌር የታጠቀች ናይጄሪያ ማለት ናት!.." ሲሉ ለሞስኮ-በዚያውም ለአፍሪካ ያላቸውን የመረረ ንቀት ገለጹ፡፡ ሞስኮ ለሰባት ዓመታት በኢኮኖሚ ውጥንቅጥ ውስጥ ቆየች፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን ወደስልጣን ሲወጡ ግን መሪዋ ብቻ ሳይሆን እጣ ፈንታዋም ተቀየረ፡፡

እኚህ ሰው በ10 ዓመታት የስልጣን ቆየታቸው ወቅት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከ350 ቢሊዮን ዶላር ወደ 3 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር አሳደጉት ፡፡ ከአውሮፓ ጋር የነበረው ዓመታዊ የንግድ ልውውጥም ወደ 453 ቢሊዮን ዶላር ተመነደገ፡፡ እንግዲህ ለእኚህ ታላቅ ሰው ተጨማሪ 10 ዓመታት ቢሰጣቸው እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደ በፊቱ በ10 እጥፍ እንኳን ባይሆን እንደው በአምስት እጥፍ ቢያሳድጉት ሩሲያ ዳግም ወደ ኢኮኖሚ ሀያልነቷ መመለሷም አይደል! .. ያውም ከአሜሪካ በግማሽ ያነሰ ሕዝብና በእጥፍ የሚሰፋ ሀገር ይዛ! እኚህ ሰው በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከአውሮፓ ጋር ያለውን ዓመታዊ የንግድ ግንኙነት በእጥፍ እንኳን ቢያድጉት ሩሲያ አሜሪካን በማፈናቀል የአውሮፓ ሕብረት ዋነኛ የንግድ አጋር ልትሆን አይደል! ይህም አሜሪካ በአውሮፓ ሕብረት ላይ ያላትን ተጽእኖ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ይሆናል፡፡

የምእራብ አውሮፓ ሀገራት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከደረሰባቸው ከፍተኛ ውድመት በኋላ ዳግም የተገነቡት የአሜሪካን ዶላር መሠረት ባደረገ የኢኮኖሚ ስርዓት ነው- ኤውሮ እንኳን ቢኖር! ለዚያ ነው የአሜሪካ ኢኮኖሚ ሲያስነጥሰው የአውሮፓ ኢኮኖሚ የሚዘረረው፡፡ ሩሲያና ቻይና የአውሮፓን የንግድ ድርሻ ከአሜሪካ መቀማት ከቻሉ ግን ነገሮች እየተቀያየሩ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ለዚያም ነው ዋሺንግተን ፋታ በሌለው ፍጥነት የሩሲያን ኢኮኖሚ ግስጋሴ ለማስቆም የወጠነችው፡፡

ይህንን ውጥን ለማሳካት በተለይ ከ2014 ወዲህ በሰበብ በአስባቡ ሩሲያ ላይ እጅግ የበዙ የኢኮኖሚ ማእቀቦችን በተናጠል ጥላለች፡፡ ዋሺንግተን ሞስኮ ላይ ማእቀብ መጣሏ ሳያንስ ከሩሲያ ጋር የሚነግዱ በርካታ የአውሮፓ ሀገራትና ኩባንያዎቻቸው በአሜሪካ እንዳይሰሩ ማድረግን ጨምሮ በወንጀል እስከመጠየቅ የደረሰችው፡፡ እንግዲህ በሌሎች ሀገራት ንግድ ውስጥ ገብቶ በወንጀል መጠየቅ ማለት የአሜሪካን ሕግ በሌሎች ሀገራት ላይ መጫን እንደሆነ ያስተውሏል፡፡

እዚህ ላይ ሉአላዊነት አበቃ ማለት ነው! ይሁንና አውሮፓ ሲሶ የሚሆነውን ነዳጅ ዘይትና 40 በመቶ የሚጠጋውን የተፈጥሮ ጋዝ ከሞስኮ በተወዳዳሪ ሂሳብ የሚገዛ በመሆኑ በሩሲያ ላይ የነዳጅ ግዢ ማእቀብ ማስጣል አልተቻለም- ይህንን ማድረግ የአውሮፓን የኢኮኖሚ ወገብ ስለሚቆርጥ! በመሆኑም አሜሪካ ከሳኡዲ አረቢያና ኳታር ተነስቶ በሶሪያ እና ቱርክ በኩል አድርጎ አውሮፓ የሚገባ የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ መስመር ለመገንባት አሰበች፡፡ ይህ የነዳጅ መስመር "ዚ ናቡኮ ላይን" ተብሎ ይጠራል፡፡ ዋሺንግተን ይህ መስመር ሳይዘረጋ በፊት የአውሮፓ ሕብረት በሩሲያ ነዳጅ ዘይት ላይ ማእቀብ እንዲጥል ያላት ውጥን ሊሳካ እንደማይችል ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡

የነዳጅ መሥመሩ መንታ ስለት ያለው መሣሪያ ነው፡፡ በአንድ በኩል አሜሪካ በአውሮፓ የኃይል ገበያ ላይ የጉሮሮውን ድርሻ የሚሰጣት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ሩሲያን ከአውሮፓ የኃይል ገበያ የምታባርርበትን ቀይ ካርድ የሚሰጣት ኃይለኛ መሣሪያ ይሆናል፡፡ ይሁንና ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ሲፈርድበት ለዘመናት የሞስኮ ወዳጅ በነበረችው ሶሪያ በኩል የግድ የሚያልፍ በመሆኑ የአሳድን አስተዳደር አንስቶ የአሜሪካ ወዳጅ በሆነ ሌላ አሻንጉሊት አስተዳደር መተካት ያስፈልጋል፡፡ የነዳጅ መስመሩ መዘርጋት የመካከለኛው ምስራቅ የነዳጅ አምራቾች ለዘመናት ሲመኙ የኖሩትን የአውሮፓ የኃይል ገበያ ደጃቸው ላይ እንደሚያመጣው ተስፋ በማድረግ አረባዊቱን ሶሪያን ከዱ! አዲዮስ የአረብ ወንድማማችነት! ብለው።

ሕዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት አሳድ ከስልጣን እንዲነሱ ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፉ! በወቅቱ የተረጋገጠ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያልነበራት ቱርክም በግዛቷ ከሚዘረጋው የነዳጅ መስመር በዓመት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የኪራይ ገቢ የሚያስገኝላት ከመሆኑም በላይ የአውሮፓ ሀገራት ለራሳቸው የኃይል አቅርቦት ሲሉ የቱርክን ደህንነት እንዲጠብቁ የሚያስገድዳቸው በመሆኑ የፕሮጀክቱ ጠቃሚነት ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በመሆም የሕዝባዊ ተቃውሞውን ንፋስ ተከትሎ ፕሬዚዳንት አሳድ ከስልጣን እንዲነሱ ጥሪ አቀረበች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ጥቂት ዓመታት አስቀድሞ የእስራኤል ወታደራዊ ሳተላይቶች በሶሪያ በረሃ ውስጥ በድብቅ ሲገነባ የነበረ የኒውክሌር ማብላያ ሕንጻን ማውደማቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢየሩሳሌም የአሳድ አስተዳደር እስኪነሳ ድረስ እንቅልፍ አልነበራትም፡፡

ኒውክሌር የታጠቀ ጎረቤት ጠላት ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት እስራኤልን ከምድረ-ገጽ ሊያጠፋ ይችላልና! የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ሀገራት ጥምረት በአንዱ አባል ሀገር ላይ የሚደረግ ወረራ በሌላው አባል ሀገር ላይ እንደተደረገ ወረራ የሚቆጥር ነው፡፡ ይሁንና በሌላ በምንም ምክንያት አንዱ አባል ሀገር ጦርነት ቢጀምር ሌሎች አባል ሀገራት በቃል ኪዳኑ ሳቢያ ወደጦርነቱ ይገባሉ፡፡ ለዚህ ነው ጥቅማቸውን ቢጎዳም ጋዳፊን ባነሳው የሊቢያው የእርስ በእርስ ጦርነት እና ምንም አይነት የሚታይ ጥቅም በማይገኝበት የአፍጋኒስታኑ ጦርነት ላይ የቃል ኪዳን ድርጅቱ አባላት ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩት፡፡

በቃ ሳር ቅጠሉ ሳይቀር የሶሪያ ጠላት ሆነ! የኃይል አሰላለፉ ከላይ በገለጽኩት መንገድ ከተሰደረ በኋላ ነው የሶሪያን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሀገሪቱ እጅግ የከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ የተደረገው፡፡ ይሁንና መልካም አስተዳደርና ሰብዓዊ መብትን በማስከበር ረገድ ከአናሳው አላዋይት ብሔር የወጡት የአሳድ ቤተሰቦች ከሚበዙት የመካከለኛው ምስራቅ መንግሥታት ይልቅ የተሻለ ሬከርድ ነበራቸው - በሶሪያ የክርስቲያኖችም ፣ የሙስሊሞችም ፣ የአራማይኮችም ሆነ የድሩዞች መብት ከሚበዙቱ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አናሳ ብሔሮች በተሻለ ይከበር ነበር፡፡

ጦርነት ውስጥ ከተገባ በኋላም አሜሪካ ውስጥ ውስጡን የሶርያ ጦር ከፍተኛ መኮንኖች ፕሬዚዳንት አሳድን እንዲከዱ መገፋፋቷን ቀጠለች፡፡ በዚያ የተነሳ በምእራባውያኑ መገናኛ ብዙሃን የሶሪያ ነጻ አውጪ ጦር ተብሎ ሲቆላጰስ የቆየው ቡድን ተወለደ፡፡ ቡድኑ ሀገራቸውን በከዱ ከፍተኛ የጦሩ መኮንኖች ተቋቁሞ ኃይማኖታዊ አክራሪዎችን በስፋት ጨምሮ የተጠናከረ ነው፡፡ ዋሺንግተን ለዚህ ድርጅት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች- በ2013 ብቻ ለድርጅቱ የሰጠችው ድጋፍ ከ120 ሚሊዮን ዶላር የዘለለ ነው፡፡

ገና ለገና ከአሳድ መውረድ በኋላ ስለሚገኘው ጥቅም ተስፋ ያደረጉት የመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ አምራች ሀገራትም ጦርነቱን በገንዘብና ጦር መሣሪያ በስፋት ደገፉ፡፡ ምንም እንኳን ራሱን የሶሪያ ነጻ አውጪ ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን የፈጸማቸው አረመኔያዊ ተግባራት እጅግ የከፉ ቢሆኑም የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን አይተው እንዳላዩ ሆኑ፡፡ በአንጻሩ የአሳድን አስተዳደር ጭራቅ አድርገው ሳሉ፡፡

የሶሪያ ነጻ አውጪ ጦር ተብሎ የተደራጀው ቡድን በርካታ የሀገሪቱን ወታደሮች የአሳድ ወታደሮች በሚል ስያሜ ጨፈጨፈ! ሀገሪቱን ከአሳድ አስተዳደር ነጻ ለማውጣት በሚል ሰበብ ያለፍርድ ግድያን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጽም ቆየ፡፡ እንዲያውም የመንግሥታቱ ድርጅት ያቋቋመው አጣሪ ቡድን ድርጅቱ እጅግ የከፋ የጦር ወንጀል መፈጸሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁንና በነአሜሪካ ጫና የጦር ወንጀሉ ሪፖርት በመጠንም ሆነ በስፋት የአሳድ መንግሥት ከፈጸመው ጋር አይመጣጠኑም የሚል ሀረግ እንዲጨመርበት ተደርጓል፡፡

የሶሪያ ጦር በውቅሩ ጠንካራ ስለነበረ በከሀዲ የጦሩ መኮንኖች የተቋቋመው የሶሪያ ነጻ አውጪ ኃይል ምንም ያህል በምእራባውያን ቴክኖሎጂና የመሣሪያ ድጋፍ ቢደረግለት መንግሥትን እንደማይጥለው ተረዱ፡፡ በመሆኑም አንድ ጊዜ የአሸባሪውን አይ ኤስ ቡድን ለማጥፋት ፣ አንድ ጊዜ ደግሞ ንጹሐንን ከጥቃት ለመጠበቅ በሚል ሰበብ በኋላ ደግሞ የሀገሪቱ የኬሚካል የጦር መሣሪያዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጅምላ ጥፋት ለማስቀረት በሚሉ ሰበቦች በደማስቆ ላይ ሙሉ ጦርነት ከፈቱ፡፡ ሀገሪቱ ላይ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማእቀብ በመጣል የሶሪያን ችግር እጅግ አባባሱት፡፡

እንግዲህ ግቡ ሌላ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ወንጀል በሰብአዊ መብት እና ዲሞክራሲ ስም የተደረገ ነው፡፡ በሶሪያ የረድኤት ድርጅቶች እንደ አሸን ተፈለፈሉ፡፡ የገንዘብ ምንጫቸው በአመዛኙ ከምእራባውያን የሚያገኙት የረድኤት ድርጅቶች ተግባራቸውን ለመከወን የምእራባውያንንም ጥቅም ማስጠበቅ እንዳለባቸው ልብ ይሏል፡፡ በአንዳንድ የረድኤት ድርጅቶች ውስጥ ሶርያውያን የማይገቡባቸው በሚስጥር ቁልፍ የሚከፈቱ ቢሮዎች ይገኙ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ የረድኤት ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ለሶርያውያን የተዘጉ ቢሮዎች ዋና ሥራቸው ከዋናው የረድኤት ስራ ውጪ የሆኑ የስለላ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ መተንተን ፣ማደራጀትና ለምእራባውያኑ ማሸጋገር ነው፡፡

በስተመጨረሻ ሩሲያ የሶሪያው እና የዩክሬኑ ጦርነት ትክክለኛ ዒላማ እርሷ መሆኗን ስትረዳ የአሳድ መንግሥት ይፋ ጥያቄ ካቀረበላት ሶሪያን ከውጪ ወረራ እንደምትታደግ ቃል ገባች- አደረገችውም! አሜሪካ መራሹ የኔቶ ጦር አምስት ዓመት ሙሉ በአውሮፕላን አይ ኤስን ሲደበድብ ቆይቶ ያላመጣውን ውጤት ሩሲያ በዘጠኝ ቀናት ድብደባ አምጥታለች፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም የአሳድ አስተዳደር ከ90 በመቶ የሚበልጠውን የሀገሪቱን ይዞታ እንዲረከብ አደረገች፡፡

እቁቡ የተበላባቸው ምእራባውያንም በሶሪያ መሠረተ ልማት ላይ ከ270 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ጥፋት ካደረሱ በኋላ ቀስ በቀስ የደማስቆንም ሆነ የነዳጅ መስመሩን ጉዳይ እያቀዘቀዙት ሄዱ፡፡ የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃንም እንደለመዱት ያለምንም ተጠያቂነት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ውሸት ሲመግቡት ቆይተው ትኩረታውን ወደ አፍጋኒስታን አደረጉ፡፡

ከሶሪያ ልንማር የሚገባን ዋነኛ ቁምነገር የሚመስለኝ የረድኤት ድርጅቶች አያያዝ እና የውጪ ሚዲያዎች እንቅስቃሴ ጉዳይ ነው፡፡ የረድኤት ድርጅቶች ዋነኛ የገንዘብ ምርጭ የአሜሪካ መንግሥት እና ምእራባውያን ናቸው፡፡ በመሆኑም በሶሪያው ጦርነት ወቅት የረድኤት ድርጅቶች እንደልብ መፋነን ምእራባውያኑ መሬት ላይ ያለ የስለላም ሆነ የሀገሪቱን ጥቅም የሚጎዳ መረጃ እንደልብ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ድርጅቶቹ ገንዘብ የሚያስገኙላቸው ፕሮጀክቶች ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው የረጂዎች ፍላጎት ሲቀየር እነርሱም የመቀየር ባህሪ አለው፡፡

በቅርቡ ቀድሞ በኢትዮጵያ ያገለገሉ የምእራብ ሀገራት አምባሳደሮች የተሳተፉበት እና በሕዝብ ምርጫ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግሥት በሕቡእ ዘመቻ ለማንሳት የተደረገው የዙም ውይይት ላይ እንደሰማችሁት ለመፈንቅለ መንግሥቱ መሳካት በኢትዮጵያ የሚገኙትን 25ቱን ትልልቅ ግብረሰናይ ድርጅቶች የመጠቀም እቅድ አለ፡፡ ይሁንና የረድኤት ድርጅቶችን መዝጋት አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች ሆነ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ሊያሳጣ ይችላል፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ ካላችሁ የረድኤት ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር የቀረበ ሚስጥራዊ ግንኙነት በመፍጠር በሀገሪቱ ላይ ምእራባውያኑ ሊያደርሱ የሚችሉትን ችግር ብቻ እየነጠሉ ቀድሞ ማክሸፍ ይቻላል፡፡

ያንን ለማድረግ በግብረሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ከሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ጋር ብቻ በየጊዜው ውይይት ማስጀመርና ከእነርሱ የሚገኙ ግብረመልሶችን መተንተን ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ለረድኤት ድርጅቶች በውጪ ምንዛሬ የሚደረጉ ልገሳዎች በሙሉ በሀገር ውስጥ ባንኮች ብቻ እንዲያልፉ ማድረግ እና ባንኮቹ ደግሞ ገንዘቡን መንዝረው ለረድኤት ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ ብር ብቻ እንዲያስረክቡ ማድረግ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚስተዋለውን የዶላር እጥረት መቀነስ ይቻላል፡፡

ሌላው ደግሞ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች አጠራጣሪ ነገሮች ሲያዩ በሚስጥር መጠቆም የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋትን ያስፈልጋል፡፡ አጠራጣሪ ስል ቀድሞ ያልነበሩ በፈረንጆች ብቻ የሚከፈቱ፣ የሚስጥር ቁልፍ ያላቸው ቢሮዎች አይነት ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ ቢሮዎች ከዋናው የረድኤት ሥራ የተገነጠለ የመረጃ ሥራ የሚሠራባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የረድኤት ድርጅቶቹን መደበኛ ሥራ ሳያስተጓጉል መንግሥት ነጥሎ አጠራጣሪ ቢሮዎችን ብቻ በድንገት ሊበረብር እና ማብራሪያ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ይህ ሥራ ሲከናወን በረድኤት ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን ሥራ የሚያሳጣ ሊሆን አይገባውም፡፡ ሚዲያን በተመለከተ ደግሞ በሶሪያው ጦርነት ላይ የነበረው ድርሻ ጨርሶ እውነትን የመዘገብ አልነበረም፡፡ የሶሪያን መንግሥት እጅግ ማጠልሸት እንጂ! ሀገራችን በገጠማት ሁኔታም የምእራብ መገናኛ ብዙሃን ድርሻ ከዚህ የተለያ አይደለም፡፡ የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን በሶሪያው ጦርነት ላይ እንደልብ እንዲዘግቡ የአሳድ መንግሥት መፍቀድ አልነበረበትም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም እውነት ከመዘገብ ይልቅ አፍራሽ በሆነ ፕሮፓጋንዳ ሥራ ላይ የተጠመዱትን መገናኛ ብዙሃን ሩሲያ እንዳደረገችው የውጪ ሀገር ወኪሎች አዋጅ አውጥቶ አደብ ሊያስይዛቸው ይገባል፡፡ ማለቴ ሀገር ቤት ቢኖሩም ባይኖሩም የሀገሪቱን ሥም ከማጠልሸት ውጪ የሚጠቅሙት ነገር ባለመኖሩ ወኪሎቻቸው አዲስ አበባ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንጂ ለኢትዮጵያ ፈቃድ እንዳያገኙ ማድረግም አንድ አማራጭ ይሆናል፡፡ በምትኩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንዲያብቡ መንግሥት ሊያግዛቸው ይገባል፡፡ አበቃሁ፡፡ በቀጣዩ እትም እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም