ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ዜጎች ለሶስት ቀናት የሚቆይ ደም ልገሳና ሃብት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተጀመረ

243

አዲስ አበባ፤ ህዳር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ለሶስት ቀናት የሚቆይ የሃብት ማሰባሰብና የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተጀመረ።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሕዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆየው መርሃ ግብር ማስጀመሪያ መድረክ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

መርሃ ግብሩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሴቶች ፎረምና አጋር አካላት ጋር ያዘጋጀው የ16ቱ ቀን የፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ  አካል እንደሆነ ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አለሚቱ ኡሙድ እንደገለጹት ድጋፉ በሚኒስቴሩ አስተባባሪነት በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ፣ በአንድ ማዕከልና ማገገሚያ ማዕከላት ለሚገኙ “እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ነው።

ሴቶችና ሕፃናትን ዕድሜና ፆታን መሰረት አድርገው ከሚፈፀሙ ጥቃቶች ለመከላከል በየዓመቱ የግንዛቤ መፍጠሪያና የንቅናቄ ስራዎች እንደሚከወኑ አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን “ሠላም ይስፈን፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም” በሚል አገራዊ መሪ ሃሳብ ከሕዳር 16 እስከ 30 ቀን 2014 በተለያዩ መርሃግብሮች እየተከናኑ ይገኛሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሚኒስቴሩ እስካሁን 100 ሚሊዮን ብር የአይነት እንዲሁም 116 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንና በቀጣይም ድጋፉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆምና ለሠብዓዊ መብት ጥሰት የተጋለጡ ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የተለያዩ አካላት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

አገር የሕልውና ፈተና በገጠማት በዚህ ወቅት ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ አኩሪ ገድል እየፈፀሙ ለሚገኙ የሠራዊት አባላትና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ‘አይዟችሁ፣ ከጎናችሁ ነን’ በማለት ደጀንነታችንን አጠናክረን እንቀጥል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተመድ የሴቶች ጉዳይ ክትትል የአፍሪካ ኅብረትና የኢትዮጵያ ተወካይ ሌቲ ቺዌራ በበኩላቸው “እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ” ዘመቻ በግጭቱ ለተጎዱ ሴቶችና ልጃገረዶች ማድረግ የምንችለውን በማድረግ ድጋፍና ተስፋ መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀንን በንግግር ከማክበር ባለፈ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እንዲቆም በተግባር የተደገፉ ስራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ስለ ሴቶችና ልጃገረዶች ግድ የሚላቸው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።   

ድጋፉን ለሁለቱ ቀናት በተለያዩ ሞሎችና በሁሉም ክፍለከተሞች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከሕዳር 30 እስከ ታህሳስ 8 ቀን 2014 በጊዮን ሆቴል በሚገኘው ግሮቭ ጋርደን ወክ ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።

ኅበረተሰቡ የታሸጉ ደረቅ ምግቦች፣ የምግብ ማብሰያና መመገቢያ ቁሳቁስ፣ ለሴቶችና ለሕፃናት የሚሆኑ አልባሳት፣ ብርድልብሶች፣ የህፃናት ወተት እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።