የፍርድ ቤቶች ሰራተኞች ለዘማች ቤተሰቦች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ

58

ባህር ዳር  ህዳር 28/2014 ዓ/ም /ኢዜአ/ አሸባሪውን ህውሓት በግንባር እየተፋለሙ ላሉ የዘማች ቤተሰቦች የሚያደርጉትን ድጋፍና እንክብካቤ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ሰራተኞች አስታወቁ።

የፍርድ ቤቶቹ ሰራተኞች፣ ባለሙያዎችና ጠበቃዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ዛሬ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰብስበዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አብየ ካሳሁን በሰብል ስብሰባው ላይ እንደሉት የውጭ ባእዳን ተላላኪ የሆኑት ህውሓትና ሸኔ በከፈቱት ጦርነት የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነት ስጋት ላይ ወድቆ ነበር።
የህልውና አደጋውን ለመመከት የክልሉ መንግስት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ሚሊሻዎች፣ የግል ባለመሳሪያዎችና ወጣቶች ተቀብለው ወደ ግንባር ግንባር መዝመታቸውን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱና በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ሰራተኞችና ጠበቆች በዛሬው እለት የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ የደጀንነት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዘማቾች ሰብል ምርት ሳይበላሽ በወቅቱ በመሰብሰብ ጭምር የሚያደርጉትን ድጋፍና እንክብካቤ አጠናክረው እምደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባለሙያ ወይዘሮ ፅዮን ተዋቸው በበኩላቸው ሀገር ለማፍረስ የመጣ ጠላትን ለመመከት የዘመቱ ወገኖችን ለማገዝ በሰብል መሰብሰብ ስራው መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
የዘማች ቤተሰቦችን የመደገፍና የመንከባከብ ተግባር የሁሉም ህዝብ ኃላፊነት በመሆኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የፍርድ ቤቱ ሰራተኛ አቶ በላይ የሽዋስ በበኩላቸው ለሀገር ክብርና ህልውና እየተዋደቀ ላለው ዘማቾች ሰብል መሰብሰብና ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብ መቻል የደጀኑ ህዝብ ትንሹ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የህልውና ጉዳይ የማንኛውም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ የዘማች ቤተሰቦችን በመንከባከብ በኩል በሚቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አስፈላጊውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በፎገራ ወረዳ ወደ ግንባር የዘመቱ አርሶ አደሮችን ማሳ ቀድሞ በመሰብሰብ ከምርት ብክነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የወረዳው የግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላክ አላምረው ገልጸዋል።

በወረዳው በተለያየ ሰብል ከለማው 625 ሄክታር የዘማቾች ማሳ ውስጥ እስካሁን 606 ሄክታር ላይ የነበረው የደረሰ ሰብል በተማሪዎች፣ በመንግስት ሰራተኞችና በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሰብሰቡን አስረድተዋል።

በፎገራ ወረዳ ቲዋዛ ቅና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አየሁ ዋለ በበኩላቸው ባለቤታቸው ሀገር ህልውና አደጋ ላይ ስትወድቅ የክተት ጥሪውን ተቀብለው መዝመታቸውን ተናግረዋል።
ባለቤታቸው ከዘመቱ በኋላ ያለሙት የሩዝ ሰብል በፍርድ ቤት ሰራተኞች መሰብሰቡ እንዳስደሰታቸውና ኩራት እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
"ስትደጋገፍና ስትረዳዳ ሀገር ትቀናለች" ያሉት ወይዘሮ አየሁ፤  ህብረተሰቡ የዘማች ቤተሰቦችን ለመደገፍ  እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም