በሕብረ ብሔራዊና ወንድማማችነት መንፈስ የኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ይቆማል

76

ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) "በሕብረ ብሔራዊና ወንድማማችነት መንፈስ የኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ይቆማል" ሲሉ የሰላም ሚንስትር ደኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ተናገሩ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሰራተኞች "ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ 16ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን አክብረዋል።

የሰላም  ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በዚሁ ወቅት ህብረ-ብሔራዊነትና ብዝሃ-ማንነት የኢትዮጵያ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም "የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴት የኔ ነው" ብሎ መቀበል እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

በዚህም በሕብረ ብሔራዊና ወንድማማችነት መንፈስ የኢትዮጵያ አንድነትን በጽኑ መሰረት ላይ እናቆማለን ነው ያሉት፡፡

''የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የሚከበረው ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው የሽብር ቡድን ድል እየተቀናጀን ባለንበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለአገራቸው ህልውና ያለ ልዩነት በአንድነት መሰለፋቸውንም ነው ያነሱት፡፡

መገናኛ ብዙሃን ሰላም አንድነትና መተሳሰብ ላይ በትኩረት በመስራት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተጀመረው መደጋገፍ ቀጣይነት እንዲኖረው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡ ሙስና እና ሌብነትን እንዲዋጋ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡

16ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በድሬዳዋ ከተማ ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም