በምዕራብ ሸዋ ዞን ተማሪዎችና መምህራን የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል እየሰበሰቡ ነው

241

አምቦ ህዳር 29/2014 (ኢዜአ) …በምዕራብ ሸዋ ዞን የሀገር ህልውናና ሉዓላዊነት ለማስከበር ወደ ግንባር ለዘመቱ የሚሊሻ አባላት ቤተሰቦች የደረሰ ሰብል በተማሪዎችና መምህራን በዘመቻ እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ተሾመ ፋና ለኢዜአ እንደገለጹት ከዞኑ 22 ወረዳዎች ከሚገኙ 80 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 94 ሺህ ተማሪዎችና መምህራን ለአንድ ሳምንት በሰብል ስብሰባው እየተሳተፉ ነው።

ተማሪዎቹና መምህራኑ የዘማች ሚሊሻዎችን ቤተሰቦች ሰብል ቅድሚያ ሰጥተው በመሰብሰብ የደጀንነት ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሰብል ስበሰባው ከተሳተፉት መካከል መምህር ታደሰ ጡሪ እንዳሉት የዘማቾችን ሰብል መሰብሰብና ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብ ሀገርን እንደ መደገፍ  ስለሆነ ሀገር ወዳዶች ሁሉ በዚህ ተግባር መሳተፍ ግድ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ህይወታቸውን ሰጥተው ወደ ግንባር ሲዘምቱ እኛ ደግሞ የእሳቸውን ፈለግ በመከተል ባለንበት ቦታ ሆነን ሀገርን መደገፍና የዘማቾችን ቤተሰቦች መንከባከብ አለብን ብለዋል።

በግንጪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ አቡሽ መገርሳ በበኩሉ ሰብሉን ከመሰብሰብ በተጨማሪ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ የተሰበሰበውን ከምረው በመሸፈን እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ከመሰብሰብ ባለፈ ወደ ግንባር በመዝመት የሀገሬን ህልውና ለማስከበርም ዝግጁ ነኝም ብሏል፡፡

ለሀገራቸው አንድነት ሲሉ ህይወታቸውን ለመገበር ወደ ግንባር ለሄዱ የሚሊሻ አባላት ሰብል መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን እስከ ግንባር ለመዝመት ዝግጁነቱን ያረጋገጠው ደግሞ የ11 ክፍል ተማሪ የሆነው ዋሲሁን ተክለማርያም ነው፡፡

ከሚማርበት አምቦ ከተማ ወደ ደንዲ ወረዳ በመሄድ የወላጆቹንና የሚሊሻ ቤተሰቦችን ማሳ ላይ የነበረን የደረሰ የጤፍና የስንዴ  ሰብል አጭዶ በመከመር እየተሳተፈ መሆኑንም ተናግሯል።

በዘመቻውም ለሀገራዊ ጥሪው ምላሽ መተባበራችንን እና አንድነታችንን ያሳያል ብሏል ተማሪ ዋሲሁን፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ቤተሰቦቻቸውንና የአካባቢውን ዘማች ሚሊሻ ቤተሰብን መርዳት እንዲችሉ መንግስት ላደረገው ጥሪ አመስግነው ከዚህ ባለፈ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈልም ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

ከአምቦ ወረዳ ልጃቸው ወደ ግንባር የዘመተው አርሶ አደር አበራ ፈይሳ በሰጡት አስተያየት ተማሪዎችና መምህራኑ ባደረጉላቸው እገዛ አመስግነዋል፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ የደረሰ የጤፍና የስንዴ ሰብላቸው በቀላሉ ታጭዶ መከመሩንም ተናግረዋል።

አርሶ አደር ጌጤ ዲሪሪሳ እንዳሉት ባለቤታቸው ሀገር ለማስከበር ወደ ግንባር መሄዳቸውን ገልጸው፤ ተማሪዎችና መምህራኑ ባደረጉላቸው እገዛ ከግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የስንዴ ሰብል ታጭዶ ተከምሯል።

በተደረገላቸው እንክብካቤና ድጋፍ መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡