የሚዛን አማን ከተማ ተማሪዎች የውጭ ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ

ሚዛን አማን ፤ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የአንዳንድ ምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ።
ተማሪዎቹ  በሰልፉ ላይ  ኢትዮጵያ  በአሸባሪ ህወሓት አትፈርስም፣ በምንችለው ሁሉ  ሀገራችንን ከጥፋት እንከላከላለን ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

 ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር ነች፣ ኢትዮጵያ በአሻንጉሊት መንግስት አትመራም፣ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ  ሉዓላዊነቷ ይከበራል፣ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት እንቃወማለን፣ 'አንገቴ ይቀላል እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም' የሚሉ መፈክሮችም በሰልፉ ላይ ከፍ  ብለው ተደምጠዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ተማሪ ጊዜወርቅ አጥናፉ እና ተመስገን አበበ  በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ሀገራችን  ክብሯና  ነጻነቷ ተጠብቆ  እንዲቀጥል እንፈልጋለን ብለዋል።

ተማሪዎች ባላቸው አቅም ሁሉ መከላከያን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ በትምህርት ቤታቸውም ለሀገር መከላከያ  ሠራት ድጋፍ  በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መምህር መንግስቱ ጌታቸው በበኩላቸው ''ስለ የኢትዮጵያ ክብርና አንድነት ስንማር አድገናል፤ አሁንም ለልጆቻችን የምናወርሳት ኢትዮጵያ ሰላሟ የተረጋገጠና የበለጸገች እንድትሆን የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ያልተገባ ጫናና እንቅስቃሴ በመቃወም ሰልፍ ወጥተናል'' ብለዋል።

መማርም ሆነ ማስተማር የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው ያሉት መምህር መንግስቱ፤ በህልውና ዘመቻው ግንባር ድረስ ተሰልፈው አሸባሪው ህወሓትን ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጌታሁን ቢኒያም  በሰልፉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የዛሬ ህጻናትና ወጣቶች ነገ የሚረከቧት ሀገር ስትነካ ድምጻቸውን ለማሰማት ያሳዩት ቁርጠኝነት ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይም ሁሉም ተማሪዎች ደም በመለገስ፣ ሀብት በማሰባሰብ ፣የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ እና ለሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነት በማጠናከር ደጀንነታቸውን እንዲገፉበት ጠይቀዋል።

ሰልፉ #NOMORE ወይም በቃ! የሚለው አለም አቀፍ ንቅናቄ በሰፊው የተንጸባረቀበት መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም