የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በድሬዳዋ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካን ጎበኙ

296

ድሬዳዋ፣ ህዳር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በድሬዳዋ አስተዳደር በ32 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካን ጎበኙ።

አፈ ጉባኤው  በድሬደዋ አስተናጋጅነት ነገ በሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ለመገኘት ድሬዳዋ ሲገቡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ከአቀባበሉ በኋላ በድሬዳዋ አስተዳደር በ32 ሄክታር መሬት ላይ በከፍተኛ ወጪ ተገነባውን “ሬደዋ” የተሽከርካሪ መገጣጠሚያን ጎብኝተዋል።

በወር 2 ሺህ 600 ባለሶስት እግር ታክሲዎችንና ታታ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥመው ፋብሪካ ከተለያዩ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረቁ 1 ሺህ 980 ወጣቶች የስራ ዕድል እንደፈጠረላቸው ተገልፆላቸዋል።

አፈ ጉባኤው አቶ አገኘሁ ተሻግር 16ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ና ህዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ “ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ  አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን የንግድና ትርኢት ባዛር ከፍተዋል።

ባዛሩን ከሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ ኢብራሂም ዑስማንና ከድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ጋር በመሆን ጎብኝተዋል።

በተጨማሪም አፈጉባኤው የድሬዳዋ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽንን የለወጥና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ተመልክተዋል።

16ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ና ህዝቦች በዓል ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ይጠበቃል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።