የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለመከላከያ ሠራዊት 70 በላይ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረገ

228

ህዳር 28/2014(ኢዜአ) በቅርቡ 11ኛ ክልል ሆኖ የተመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለመከላከያ ሠራዊት 72 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረገ።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንም በተመሳሳይ 28 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አበርክቷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 60 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 1 ሺህ 170 ሰንጋ ፣ 128 በግና ፍየል ጨምሮ የተለያየ ስንቅ እና 12 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፋ አድርጓል።

ድጋፉን ያስረከቡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ማስረሻ በላቸው ኢትዮጵያ ላይ ስለተቃጣው አንድነትን የመሸርሸር የውስጥና የውጭ ሴራ አንስተዋል።

ይሁንና ይህን ሴራ ኢትዮጵያዊን በተባበረ ክንድ እየመከቱት እንደሆነም ተናግረዋል።

በተለይም የአገር መከላከያ ሠራዊት በዋናነት ከፊት ሆና ሕይወቱን እየሰጠ በመሆኑ እሱን መደገፍ አገራዊ ግዴታ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን 28 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አድርጓል።

ኮሚሽነር ደበላ ቃበታ በድጋፍ ርክክቡ ላይ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስልጣን ላይ በነበረ ጊዜም ሕገወጥ ንግድ በመፈጸም አገሪቷን ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ጥሏት እንደነበረ አስታውሰዋል።

ተቋሙ ከተሰጠው ሃላፊነት በተጨማሪ ማኅበራዊ ሃላፊነቱን በተለያየ መልኩ እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ባለፈው አንድ ዓመት ለመከላከያ ሠራዊት 160 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በዛሬው ድጋፍም 20 ሚሊዮን ብር እና ስምንት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አልባሳትን ለመከላከያ ሠራዊቱ አበርክቷል ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ድጋፍ ካደረጉ መካከል የኢትዮጵያ አንጋፋ አትሌቶች ማኅበር አንዱ ነው።

ማኅበሩ 100 ሺህ ብር የሚያወጡ አልባሳትን ያበረከተ ሲሆን ድጋፉ በዚህ እንደማያቆምና ቀጣይ እንደሆነ አትሌት ጌጤ ዋሚ ተናግራለች።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ሠራዊቱ እያስመዘገባ ለሚገኘው ድል የሕዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ አገሩን ለመታደግ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነትና አንድነት በየተሰማራበት የሙያ መስክም በመድገም ለኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።