በአሸባሪው የህወሃት ወረራ ምክንያት የባከነውን ምርት ለማካካስ የመስኖና በልግ ሰብል ምርታማነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል

221

ህዳር 28/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሃት ወረራ ምክንያት የባከነውን ምርት ለማካካስ የመስኖና በልግ ሰብል ምርታማነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የግብርና ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ዓመታዊ የ2014 ዕቅድን ገምግሟል።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ በ2014 የምረት ዘመን 691 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ከዚህም ውስጥ 375 ሚሊየን  ኩንታሉ በመኽር ወቅት ለመሰበሰብ የታቀደ መሆኑን ገልጸው፤ በአሸባሪው ህወሃት ወረራና በድርቅ ምክንያት የባከነውን ምርት ለማካከስ በበልግና በመስኖ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በበልግ 50 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል እንዲሁም በበጋ መስኖ ደግሞ 16 ሚሊየን ኩንታል ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

‘አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም’ በማለት ንቅናቄ ዕቅድ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ጦርነቱ በነበራቸው አካባቢዎች ካለፈው ዓመት 36 በመቶ እድገት ያለው የበልግ ምርት ለመሰበሰብ መታቀዱን ነው የተናገሩት።

ይህም ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚፈጠረውን ተዕጽኖ ለመቋቋም እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ከግብርና ሰብሎች መካከልም በመኸር፣በበልግና በመስኖ ወራት በአትክልትና ፍራፍሬ እና ስራ ስሮችን 2 መቶ 10 ሚሊየን ኩንታል፣ በቡናና ሻይና ቅመማ ቅመም 13 ሚሊየን ኩንታል ለማምረት ታቅዷል።

ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአትክልታና ፍራፍሬ 25 በመቶ፣ በቡና እና ሻይ 6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ ለመሰበሰብ የታቀደው ዕቅድ ከአገሪቷ አሁናዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማደረግ ምርትና ምርታማናት ለማሳደግ የትኩረት አቅጣጫ እንደተሰጠ ተናግረዋል።

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ  ሰብሳቢ  አቶ ሰለሞን ላሊ በቀረበው በበኩላቸው እቅዱ ጦርነቱ የሚያስከትለውን ችግር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድህነትን ለማሸነፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም በመስኖና በበልግ ወራት ስራዎችን በስፋት በመስራት ከድህነትና ለመላቅቅ የተጀመረውን አገራዊ ጥረት ማጎልበት ይገባል ብለዋል።

ዕቅዱ ካለፈው የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር በመጠን የተሻለ መሆኑን በበጎ መልኩ አንስተው፤ አሁናዊ ችግሮችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የተጠሪ ተቋማት ቅንጅታዊ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።