የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾችን በማስፋት አቅርቦትን ለማሻሻል ይሰራል

224

አዲስ አበባ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾችን በማስፋት የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማኅበራዊ፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሚኒስቴሩን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡  

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ባለፈው በጀት ዓመት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ጋር በተያያዘ መድሃኒቶችን በሚፈለገው ደረጃ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ስራ ላይ እክል ተፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾችን የማስፋት ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

የመድሃኒት እጥረት ለመፍታት የጤና መድኅን ሥርዓት ተደራሽነትን የማስፋት ሥራ እንደሚጠናከርም እንዲሁ፡፡

በዚህም የጤና መድኅን አባላት መድሃኒት የማግኘት መብታቸውን እንዲጠይቁ ስለሚያደርግ በድጎማም ሆነ በሌሎች አማራጮች መድሃኒት እንዲገዛ እድል ይሰጣል ብለዋል።

የጤና መድህን አባላት የሚያደርጉት መዋጮ ለመድሃኒት ግዥ የሚሆን የፋይናንስ እጥረት በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከውጭ ገብተው ብልሽት የሚያጋጥማቸው የሕክምና መሣሪያች በአገር በቀል ባለሙያዎች እንዲጠገኑ የማድርግ ሥራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በጦርነት ምክንያት የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ሥራም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ለእቅዱ ተግባራዊነት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍታሃዊነት የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡