የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እንደ አድዋው ድል ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው ለማሰለፍ ያስቻለ ነው

314

ጎንደር፤ ህዳር 28/2014(ኢዜአ) የህልውና ዘመቻውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በግንባር ለመምራታቸው እንደ አድዋው ድል ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ ከጎናቸው ለማሰለፍ ያስቻለ ነው ይላሉ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን፡፡

ምሁራኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት የውክልና ጦርነት   ለአፍሪካውያን ያበረከተችውን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ለማደብዘዝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በጥቁር ህዝቦች ታሪክ የነጭ ቅኝ ገዢዎችን ወረራ መክታ በመመለስ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች የመጀሪያዋ አፍሪካዊ ሀገር  ነች ሲሉ የዩኒቨርሲቲው  የህግ መምህር አቶ መኳንንት ዱቤ ይገልጻሉ።

ዛሬ ላይ የተከፈተባት የምዕራባዊያን የውክልና ጦርነት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የዳግም የቅኝ አገዛዝ  የባርነት አስተሳሰብ መገለጫ ነው ይላሉ።

የምዕራባውያን የእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ “ኒዮ ኮሎኒያሊዝም” አስተሳሳብና ፍላጎት በመዋጋት ኢትዮጵያ የቅኝ ገዢዎችን የባርነት ቀንበር በጽኑ ታግላ አሸቀንጥራ በመጣል ነጻነቷን አስከብራ የቆየች አፍሪካዊት ሀገር መሆኗንም አመላክተዋል።

አንዳንድ የምዕራባዊያን  ሀገራት አፍሪካን የመቀራመት ዝንባሌያቸው ዳግም ሌላ ቅርጽ እየያዘ መምጣቱን ጠቁመው፤  በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡

በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሽፋን በሀገራት የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት የሚደረጉ ጫናዎች የአሜሪካና ተከታዮቹዋ ታሪካዊ መገለጫዎች መሆናቸውን ኢትዮጵያ ተጨባጭ ማስረጃ እንደምትሆን የህግ ምሁሩ አስረድተዋል፡፡

”ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የተነሱባትን የውጪ ወራሪ ጠላቶች ድባቅ መታ አሳፍራ በመመለስ በኩል ዛሬ የተጀመረ የተጋድሎ ታሪክ አይደለም” ያሉት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ስለሺ ዋለልኝ  ናቸው፡፡  

ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ተወራ በነበረችበት ወቅትም ቢሆን አጼ ሃይለስላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን መድረክ ላይ በመንግስታቱ መሪዎች ፊት ያቀረቡት የህግ የበላይነት ጥያቄ ፍትህ በሌለበት ሁኔታ ምላሽ ተነፍጎት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዘመኑ ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደሉ ለነጻነታቸው በከፈሉት መስዋእትነት ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የጥቁር   ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል በመሆን ጎልታ እንደወጣች የህግና የታሪክ ድርሳኖች አመላካች ናቸው ብለዋል፡፡

ዛሬም አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን የእነሱ ተላላኪ በሆነው አሸባሪው የህወሃት ቡድን አስፈጻሚነት የከፈቱብን ጦርነት በህዝቦዊ ተጋድሎና በመሪዎቹዋ ቁርጠኛ አመራር  ዳግም የሚቀለበስበት ጊዜ እሩቅ አይደለም ነው ያሉት አቶ ስለሺ፡፡

ኢትዮጵያ ዘመናት በዘለቀው የነጻነት ታሪኳ ለወራሪዎች ተንበርክካ የማታውቅ ይልቁንም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ የነጻነት መንገድ የጠረገች የኩሩ ህዝቦች ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የአንዳንድ ምዕራባዊያን ድብቅ ሴራ በአለም አደባባዮች እያወገዙና እያጋለጡ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስና አስተሳሰብን የአለም ጥቁር ህዝቦች ትግሉን እንዲቀላቀሉ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።

በህልውና ዘመቻው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ አህመድ በግንባር ተገኝተው በሰጡት በሳል አመራር የፀጥታ ሃይሉ በጠንካራ አሸናፊነት ወኔ እየገሰገሰ በሽብር ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰና ታላቅ ድል እያስመዘገበ መሆኑ ይታወቃል።