የአኝዋሃ ዞን ለተፈናቃዮች 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ አሰባሰበ

51

ጋምቤላ ህዳር 28/2024( ኢዜአ)  በጋምቤላ ክልል የአኝዋሃ ዞን በአሸባሪው ህወሀት ወራሪ ሀይል በአፋርና በአማራ ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የዓይነት ድጋፍ ማሰባሰቡን አስታወቀ።
የዞኑ አስተዳደርና ህዝብ የህወሓት የሽብር ቡድን እኩይ ተግባር እስኪቀለበስ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡቦንግ ኡጁሉ ለኢዜአ እንደገለጹት የዓይነት ድጋፉ የተሰበሰበው በዞኑ ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች ነው።

የተሰበሰበው ድጋፍ 1 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ በቆሎ፣ ሩዝና ማካሮኒ ጨምሮ የምግብ ዘይት ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

"የአፋርና የአማራ ህዝብ ችግር የጋምቤላ ህዝብ  ጭምር በመሆኑ አስተዳደሩ ድጋፉን አሰባስቧል" ብለዋል።

ድጋፉን በቀጣይ ሳምንት ወደ ቦታው ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

የዞኑ አስተዳድርና ህዝብ ካሁን በፊት ለሀገር መከላከያ ስራዊት ያለውን ደጀንነት ለመግለጽ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት በዞኑ ብሎም በክልሉ ሲፈጸም ከነበረው ግፍና በደል በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ስም የዞኑን መሬት በመቀራመትና መሬቱን ለባንክ በማያዣነት በመጠቀም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዝብ ዘርፎ መጥፋቱን ተናግረዋል።

የህሽብር ቡድኑ እኩይ ሴራና ተግባር እስኪቀለበስ የዞኑ አስተዳደርና ህዝብ ለህልውና ዘመቻው የሚያደርጉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና አስተዳደሪው አስታውቀዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም