ኢትዮጵያ መጥተን እስካሁን ያጋጠመን ችግር የለም - የውጭ ቱሪስቶች

63

ጂንካ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ መጥተን እስካሁን ያጋጠመን ምንም ዓይነት ችግር የለም፤ በውጭ ሚዲያዎች ስለሀገሪቱ የሚሰራጨው ዘገባ ፍፁም የተሳሳተ ነው ሲሉ ደቡብ ኦሞን እየጎበኙ ያሉ የውጭ ቱሪስቶች አረጋገጡ።

ደቡብ ኦሞ ለጉብኝት  የመጡት ሚስተር ጉንሳሎ ሳንታማሪያ ፑሌ በስፔን ማድሪድ የፎቶ ትራቪል ድርጅት ዳይሬክተር   ናቸው።

ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ስለሀገሪቱ  በምዕራባዊያን ሚዲያ የሚሰራጨው ዘገባ አስደንጋጭ እንደነበር ነው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የተናገሩት።  

በዚህም ምክንያት ኤምባሲዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ቢገፋፏቸውም ኢትዮጵያ በአካል ተገኝተው የተመለከቱት ግን  እነሱ ከሚሉት ፍፁም የተለየ ሰላማዊ እንደሆነ ነው ያረጋገጡት።

ከስፔን ለጉብኝት የመጡት ቪሴንቲያ ፓሪሲዮ በበኩላቸው፤  ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ከሀገራቸው መንግስት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አስታውሰዋል።

ሆኖም አስጎብኚ ድርጅቱ  ኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ በማቅረቡ ካለምንም ስጋት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንደቻሉ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ መጥተን እስካሁን ያጋጠመን ምንም ዓይነት ችግር የለም፤ በተለይ በውጭ ሚዲያዎች ስለሀገሪቱ የሚሰራጨው ዘገባ  ፍፁም የተሳሳተ እንደሆነ የዓይን እማኝ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታችን በፊት የሀገሪቱ ዋና ከተማን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ጦርነት እንዳለ ይነገረን ነበር የሚሉት ደግሞ ሌላው ስፔናዊ ራውል ካቻዎኦሴስ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በቀር በሁሉም በተንቀሳቀሱባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ተመልክተዋል።

በውጭ ሀገር የሚገኙ ዜጎች በምዕራባውያን ሚዲያዎች በሚሰራጨው የተሳሳተ መረጃ ስለሀገራችን ያላቸው እይታ የተዛባ ነበር ያሉት ደግሞ  የጣይቱ ቱር ኤንድ ትራቭል አስጎብኚ አቶ ወንድወሰን ታደሰ ናቸው።

ሆኖም በውጭ ስለሀገራችን ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል በዲፕሎማሲው መስክ ጠንካራ ስራዎች በመከናወናቸው የተወጠነውን የጥፋት ሴራ ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።

አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  እንዲሁም ኤርትራዊያን በተለያዩ ሀገራት ከተሞች በበቃ ዘመቻ “ #NoMore" በሰላማዊ ሰልፍ  እየገለጹ፤ መንግስትም በዲፕሎማሲው መስክ እያደረገ  ያለው እንቅስቀሴ  ለውጥ እያመጣ መሆኑን የውጭ ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን መምጣት አንዱ ማሳያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ያቀረቡትን “1 ሚሊዮን ሰዎች በሀገር ቤት” ጥሪን ተከትሎ ጉዞ የጀመሩና የመጡም በመኖራቸው ይህም ምዕራባዊያን ሀገራትና ሚዲያዎቻቸው በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም