ትዊተር የኢትዮጵያን ድምጽ ለማፈን እየወሰደ ያለውን እርምጃ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በሳን ፍራንሲስኮ ይካሄዳል

86

ህዳር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የማህበራዊ ትስስር ገጹ ‘ትዊተር’ የኢትዮጵያን ድምጽ ለማፈን እየወሰደ ያለውን እርምጃ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ የፊታችን አርብ ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

ሰልፉ በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ከምሽቱ ሶስት ሰአት ጀምሮ እንደሚካሄድ የሰልፉ አስተባበሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ ለኢዜአ ገልጿል።

መነሻውን 'ሀርማን ፕላዛ' ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በማድረግ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ በሚገኘው የትዊተር ዋና መስሪያ ቤት በማቅናት ቀጥሎ ወደ ከተማው ምክር ቤት በማምራት የሚካሄደው ሰልፍ፤ ትዊተር የኢትዮጵያን እውነት የሚያስረዱ ገጾችና የግለሰብ 'አካውንቶችን' መዝጋቱ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለውና ኩባንያው ከዚህ ተግባሩ እንዲቆጠብ ጥሪ የሚቀርብበት ነው።

የኢትዮጵያውያንን እንቅስቃሴ የመገደብ ተግባር ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነ በማስገንዘብና በማውገዝ የተዘጉ ገጾችና የግለሰብ 'አካውንቶችን እንዲከፈቱ ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ አርቲስት ተስፋዬ ገልጿል።

የትዊተር አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓራግ አግራዋል ኩባንያቸው እየወሰደ ያለውን የተሳሳተ እርምጃ እንዲያቆም ከሰልፈኞቹ መልዕክት ይተላለፍላቸዋል ብሏል።

ሰልፈኞቹ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ምክር ቤት በማቅናት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫናና የምትወስዳቸውን እርምጃዎች በማውገዝ ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ አመልክቷል።

በምክር ቤቱ ለሚገኙ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና ታቁም የሚል መልዕክት የያዘ ደብዳቤ እንደሚሰጣቸውም ገልጿል።

ሰልፈኞቹ በሚጓዙባቸው አካባቢዎች የአሜሪካ ዜጎች የኢትዮጵያን እውነታ የሚያስረዱ በራሪ ወረቀቶችን እንደሚሰጡም ተናግሯል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በሰሜን ካሊፎርኒያ በሚገኙት በሳን ፍራንሲስኮ፣ ኦክላንድ፣ ሳክራሜንቶና ሳን ሆዜ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ አርቲስት ተስፋዬ አመልክቷል።

ሰልፉ የ'በቃ' ወይም '#NoMore' ዘመቻ አካል ሲሆን፤ አዘጋጆቹ በሰሜን ካሊፎርኒያ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንደሆኑ ተገልጿል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም