በአሸባሪው ህወሃት ቡድን የወደሙ የውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ እየተሰራ ነው

73

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን የወደሙ የውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መገባቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢታፋ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።  

በተለይም በውሃና በኤሌክትሪክ ግዙፍ የመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው፤ እነዚህን መሰረተ ልማቶች ለመጠገን ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውሃና ኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ወደ ሥራ መግባቱን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት ዘርፈ ብዙ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያለው ፈተና ከባድና ከወዲሁ ልንገታው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የልማት አጋር ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን በሚፈለገው አግባብ እየደገፉ አለመሆኑንም አንስተዋል።

ለአብነትም የእንግሊዝ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም /ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ/ የያዛቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች በማጓተት ኢትዮጵያ ላይ ጫና የመፍጠር አዝማሚያዎችን ማሳየቱን ጠቁመዋል።

"ነገር ግን ይህ ሊሆን የማይችል ነው፣ በጦር ግንባሮች እየተገኙ ያሉት ድሎች በልማትም ይደገማል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውሃን ጨምሮ ያሏትን ሃብቶች በሚገባ እንድትጠቀም ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ለዚህም ''በተለየ ሁኔታ ሀገር በቀል የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የሙከራ ሂደት ላይ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም በዝናብ ወቅት ዜጎች በቤታቸው ውሃ መያዝ፣ ማጠራቀም፣ ማጣራትና መጠቀም የሚያስችላቸው ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የተጋረጠባትን የሕልውን አደጋ በአሸናፊነት እንድታጠናቅቅ የኢትዮጵያን እውነታ የማሳወቅ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም