ለዘማች ቤተሰቦች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

75

አሰላ፤ ህዳር 27/2014(ኢዜአ) በአርሲ ዞን ሙኔሳ ወረዳ ሀገርን ለማዳን ወደ ግንባር ለዘመቱ አባላት ቤተሰቦች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ።

የሙኔሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አማን ሻቁሮም ፤ዛሬ ለዘማች ቤተሰቦች ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 130 ኩንታል ስንዴና ለ130 የዘማች ቤተሰብና ልጆቻቸው የተለያየ አልባሳት ይገኙበታል።

 ይህንን ጨምሮ ድጋፉ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ገልጸው፤ ሀገራችንን ከወራሪ ሃይል ለመታደግ  ለዘመቱ አባላት ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሶፊያ ሃጂ ኦሊቃ በሰጡት አስተያየት፤  ባለቤታቸው ከሀገር የሚበልጥ  ምንም የለም በማለት 11 ልጆቹን ትቶ ሀገር ለማዳን ወደ ግንባር ዘምቷል ብለዋል።

የአካባቢው አስተዳደርም ከህብረተሰቡ ገንዘብ በማሰባሰብ የነበረንን የሳር ቤት ወደ ቆርቆሮ አሳድገውልን እየኖርንበት ነው፤ ዛሬ ደግሞ በወረዳው ተወላጆች አንድ ኩንታል ስንዴና ለሁሉም ልጆቼ ልብስ ድጋፍ ተደርጎልናል ነው ያሉት።

ባለቤቴ ቀድሞ ሲሄድ አባታችን ዘምቶ እኛ አንቀርም፤ ሀገራችን  እየፈረሰች ቁጭ ብለን አናይም ብለው  ልጆቻቸውም እንደዘመቱ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ደስታ ደበል ናቸው።

ማህበረሰቡና አስተዳደሩ ከጎናቸው ሆነው ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ወይዘሮ ደስታ ፤እኛም በደጀንነት የሚጠበቅብንን ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም ብለዋል።

ድጋፉ በተደረገበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሳ ፎሮ እንደገለጹት፤ በዞኑ በሚገኙ 25 ወረዳዎችና በሶስቱ የከተማ አስተዳደሮች ለዘማች ቤተሰብ ቅድሚያ በመስጠት የደረሰን ሰብል በወቅቱ ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ።

ለዘማች ቤተሰቦች የደረሰ ሰብል ከመሰብሰብ ባለፈ ቤታቸው እንዲታደስ፣ አልባሳትና የምግብ እህል ጭምር ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን የመስኖ መሬት ያላቸው ማሳቸውን በማረስ በቆላ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲለማ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እያቀረብንላቸው ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም