ወጣቶች በሚያስፈልገው ድጋፍ ሁሉ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጎን እንቆማለን አሉ

58

ጭሮ፤ህዳር 27/2014(ኢዜአ)---የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጎን እንደሚቆሙ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ወጣቶች ገለፁ።

የሀገራቸው ሉዓላዊነትና ህልውና መደፈር ቁጭት ያሳደረባቸው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ወጣቶች ለሀገር ጥሪ ቅድሚያ ሰጥተው የሚፈለግባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኤክራም ጣሃ የዞኑ ወጣቶች አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለመበተን የደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና  አደጋ ለመቀልበስ ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዞኑ ወጣቶች እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮን በማክሸፍ የሀገር ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተደረገ ባለው ሁሉን አቀፍ ትግል ወጣቶች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ወጣት ሙዐዝ መሀመድ እንዳለው የአገሪቱ ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስ የሚፈለግበትን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ እንደሆነ ተናግሯል።

ወጣት ሙዐዝ ራሱን ወገኑንና ሀገሩን ከጥፋት ኃይሎች ለመታደግ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን ለመደገፍ መነሳቱን ተናግሯል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጎን በመሰለፍ አሸባሪው ቡድን ከደቀነው ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ሀገራቸውን ለመታደግ  አስፈላጊውን ሁሉ መስዕዋት ለመክፈል መዘጋጀቱን አረጋግጧል፡፡

ወጣት ደጀኔ ተፈራ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሀገርን ከብተና ለመታደግ በአውደ ግንባር  መገኘታቸው በሀገራዊ ስሜትና ወኔ የእሳቸውን አርዓያነት ተከትሎ የድርሻውን ለመወጣት ወስኗል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ አካባቢውን በመጠበቅ ወጣቶች ደግሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል ለሀገራቸው ዘብ እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም