የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

269

ደብረብርሀን፤ ህዳር 27/2014 (ኢዜአ) የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የዓይነት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ያስረከቡት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደገለጹት፤ ድጋፉ የተገኘው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስሩ ከሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር  ያሰባሰቡት ነው።

ከድጋፉ ውስጥም  ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚውል ስምንት ሰንጋ በሬዎች እና  1 ሺህ  600 እሽግ ውሃ  ይገኙበታል።

ለተፈናቃይ ወገኖች ደግሞ 25 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ ባለ 5 ሊትር 100 ጀሪካን ዘይት፣  200 ፍራሽ ፣100 ብርድ ልብስ፣ የንጽህና መጠበቂያዎችና አልባሳት አበርክተዋል።

የሀገር ሰላም እስኪረጋገጥ እና ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉ ተጠናከሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

ድጋፉን ከተረከቡት መካከል ብርጋዴል ጀኔራል ጠቅለው ክብረት በበኩላቸው፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የትራንስፖርት ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ባለሀብቱን በማስተባበር ሠራዊቱ ለግዳጅ የሚፈልገውን ተሽከርካሪ በማቅረብ በኩል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚመሰገን ነው ብለዋል።

ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር በዓይነት ያደረገው ድጋፍ ለሠራዊቱ ሞራልና ብርታት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደ አማኑኤል፤  አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሃን ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በዞኑ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸው፤ ተፈናቃይ ወገኖችን ለማገዝ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የወገን ጦር ባስዝመዘገበው ድል አካባቢዎች ከወራሪው ነጻ በመውጣታቸው ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት አካበቢ ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለተፈናቃዮች በተለያዩ አካላት የሚደረገው ድጋፍ  ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።