በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው

58

ኢዜአ ህዳር 28/2014/ኢዜአ/ በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ የፊታችን አርብ ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

ሰልፉ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ያልተገባ ጫና በመቃወም እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዋሺንግተን ግብረ_ሃይል አባል አቶ ከባዱ በላቸው ሰልፉ በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሰልፉ መነሻውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አድርጎ የአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ወደ ሆነው 'ካፒቶል ሂል' መድረሻውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሰልፈኞቹ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ያልተገባ ጫና የሚቃወሙ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉም አመልክተዋል።

ሰልፈኞቹ አሸባሪው ሕወሓት እየፈጸማቸው ያሉ አሰቃቂ ድርጊቶች እና የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያሰራጯቸውን ሐሰተኛ መረጃዎችን እንደሚያወግዙም ገልጸዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሰልፉ ላይ በሕልውና ማስከበር ዘመቻው ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መቆማቸውን የሚገልጹበት መሆኑንም ነው አቶ ከባዱ ያስረዱት።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና እንድታቆም የሚያስገነዝብ ደብዳቤ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

ከአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አንስቶ እስከ 'ካፒቶል ሂል' በሚደረገው የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ለአሜሪካ ዜጎች በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎችን የያዙ በራሪ ወረቀቶች እንደሚበተንም አመልክተዋል።

በሰልፉ ላይ በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ከባዱ ያብራሩት።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደቀረቡላቸውም አመልክተዋል።

ዳያስፖራው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን ጨምሮ እያከናወናቸው ባሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች የተወሰኑ ሴናተሮችና የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ላይ እያሳዩ ያለው አቋም መሻሻል እየታየበት መሆኑንም ነው የገለጹት።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ በተለያዩ አማራጮች የአሜሪካ መንግስት ላይ ጫና ማድረጉን እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም እንዲሁ።

የፊታችን አርብ ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ "የበቃ" ወይም '#NoMore' ዘመቻ አካል ሲሆን ሰልፉን የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዋሺንግተን ግብረ ሃይል ከተለያዩ ተቋሞችና አገር ወዳጆች በጋራ እንዳዘጋጁት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም