የሚገጥሙን ፈተናዎች ይበልጥ ያጠነክሩናል እንጂ ፈጽሞ ሊጥሉን አይችሉም

55

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የሚገጥሙን ፈተናዎች ይበልጥ ያጠነክሩናል እንጂ ፈጽሞ ሊጥሉን አይችሉም" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባዋ ይህን ያሉት የዘማች ቤተሰብ ሰብል ለመሰብሰብ ለሚሄዱ የትምህርት ማህበረሰቡ በተደረገው የሽኝት መር ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

መንግሥት ለአንድ ሳምንት ትምህርት ተዘግቶ ተማሪዎች የአርሶ አደሩን ሰብል እንዲሰበስቡ አቅጣጫ ማስቀመጡ የሚታወስ ነው።

በአቅጣጫው መሰረት ተማሪዎቹ ሰብል በመሰብሰብ፣ ለመከለከያ ሰራዊት ደም በመለገስ እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦችን በመጠየቅና በማገዝ የሚያሳተፉ ይሆናል።   

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም ''እናንተ ተማሪዎች የምታካሂዱት ሰብል የመሰብሰብ ዘመቻ አገሪቷ በኢኮኖሚ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት በማገዝ በኩል አውንታዊ ፋይዳ አለው'' ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ የምትገነባው በልጆቿ የተባበረ ክንድ እንጂ በልመና አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን የመገንባቱ ስራ የሁሉንም ዜጋ ትብብር እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡

ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ የሚገጥሙን ፈተናዎች ይበልጥ ያጠነክሩናል እንጂ ፈጽሞ አይጥሉንም   ነው ያሉት።

እንደ ከንቲበዋ ገለጻ፤ ተማሪዎች አገር ተረካቢዎች መሆናቸውን ተገንዝበው በእወቅትና ቴክኖሎጂ ራሳቸውን ማነጽ አለባቸው።

''የገበሬውን ሰብል ስትሰበስቡ ኢትዮጵያን እየገነባችሁ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል'' ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው ወቅቱ በህብረትና ትብብር አገር የማዳን ስራ ማከናወን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ የትምህርት ማህበረሰቡ የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የትምህርት ማህበረሰቡ ለህልውና ዘመቻው 100 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

በተጨማሪ የመዲናዋ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብና በማገዝ ሥራ ላይ እንደሚሳተፉ አብራርተዋል።

ደም ልገሳ እና የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ጨምሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት ኢትዮጵዊነትን የሚያጎሉ መርሃ ግብሮች እንደሚተገበሩም አስረድተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተማሪዎች በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ዋጋ እየከፈለ የሚገኘውን ሰራዊት ቤተሰብ  ሰብል በመሰብሰብ ማገዝ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ትንሹ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

ከእቴጌ መነን ሴቶች ልጃገረዶች ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ሌንሳ ብርሃኑ በበኩሏ የሰራዊቱን ቤተሰብ በማገዝ የማሳተፍ እድል በማግኘቷ መደሰቷን ተናግራለች፡፡

ለኢትዮጵያ ሲሉ ቤተሰባቸውን ጥለው ግንባር ለዘመቱ ወገኖቻቸንን አለሁ ማለት አለብን ብላለች።  

ደጃዝማች ወንድራድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ምህረት መኮንን በመርሃ ግብሩ የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም