ለመከላከያ ሰራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን

195

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንና የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

የተቋማቱ ሠራተኞችና አመራሮች ለመከላከያ ሠራዊቱ የደም ልገሳ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፤ የመከላከያ ሰራዊት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የኢትዮጵያን ህልውና እያስጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሰራዊቱን መደገፍ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

የባለስልጣኑ አመራሮችና ሰራተኞች ይህን በመገንዘብ ለሰራዊቱ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የደም ልገሳ መርሃ-ግብሩም የዚሁ ድጋፍ አካል ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የባለስልጣኑ ሰራተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ሁሉም ዜጋ ደም ከመለገስ ባሻገር  ለመከላከያ ሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ደጀንነቱን በተግባር ማሳየት እንዳለበት ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተቋሙ ሰራተኞችም ለሰራዊቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡