ትናንት ዛሬ አይደለም

511

ከቀደሰ ተክሌ (ኢዜአ) 


ወታደር ዮሐንስ በቀለ በ1980 ዓ.ም ነበር የውትድርና ስልጠና ወስደው በደርግ ዘመን ወደ ጦር ግንባር የዘመቱት። ያኔ ሲዋጉ የነበሩት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ሲሆን ተመተው በመቁሰላቸው ተማረከው እንደነበር ይናገራሉ። እርሳቸው በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የነበረው ሥርዓትና ጫና በመከላከያ እንዲቆዩ አላደረጋቸውምና በራሳቸው ፍላጎት ከሰራዊቱ ራሳቸውን አገለሉ።

በመከላከያ ውስጥ በብሔር ምክንያት የበላይነትና የበታችነት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው የማዕረግ ዕድገት ለማግኘት እንደ መስፈርት የሚታየው ትግርኛ ቋንቋ መናገር ነበር ይላሉ። በዚህም ምክንያት ከታችኛው እስከ ላይኛው ማዕረግ ላይ የሚገኙት አለቆች ከአንድ ብሔር የተወጣጡ ናቸው።

የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ተጠበቀ ተብሎ በሚነዛበት የህወሓት ዘመነ ስልጣን “እኔ የመገናኛ ሬዲዮ ኦፕሬተር ብሆንም በብሔር ሰበብ መገናኛ ሬዲዮ አንድም ቀን ሳልነካ ነው የወጣሁት” ብለዋል። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ የመረጃ ልውውጥ የሚደረገው በማንሰማው የትግረኛ ቋንቋ መሆኑ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። አሸባሪው ይህን ሁሉ ሴራ በመከላከያ ቤት ሲሰራ የዛሬውን ጦርነት በማሰብ ነው ሲሉም ያክላሉ።

“እኛ ተዋግተን አሸንፈን እንደገባን ሁሉ ኢትዮጵያን መምራት የሚፈልግ ሌላ አካል ከመጣ በጦርነት ስለሆነ የሚገባው ራሳችሁን ለዛ ጦርነት አዘጋጁ” የሚል መመሪያ ይሰጥ እንደነበር ተናግረዋል።

የእነርሱ የሆነ ሰው ለትምህርት እየተላከ ሌላው የኢትዮጵያ ልጅ ለግዳጅ እንዲዘምት ግዴታ ይሰጠዋል፤ የሚሰራ ሌላ የሚሸላለሙት እነርሱ ናቸው። አሁን ለከፈተው ጦርነት 27 ዓመት ሙሉ ዝግጅት አድርጓል ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያ ናትና አይችሏትም።

አሥር አለቃ ሰቦቃ ድንቁ ዕድሜያቸው 61 ሲሆን፤  በደርግ ዘመን በ1972 ዓ.ም ዘምተው  ለኢትዮጵያ ሲዋጉ ነበር። ጦርነቱን አሸባሪው ህወሓት በተንኮልና እጅ ጥምዘዛ በማሸነፍ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር በግንባር ገጥሞ የተዋጋበት ጊዜ ብዙ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። በገንዘብና ፕሮፓጋንዳ አራት ኪሎ ደረሰ እንጂ ተዋግቶ አለመሆኑንም አረጋግጠዋል።

ጁንታው ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት መከላከያን በብሔር ከፋፍሎ እንደነበር ገልጸው፤ በየጋንታ ሦስት ሦስት ሰላይ ይሰገሰጋል፤ እነሱ እኛን ይጠብቃሉ በማለት የነበረውን ጫና ያስታውሳሉ። ኋላ ኋላ ግን መከላከያን የማዳከም ሃሳብ እውን ለማድረግ አንድ ጋንታ(ሻለቃ) መከላከያን በአንድ ጊዜ በተነ። ያ የተበተነው ወታደር ሙሉ በሙሉ የሌላ ብሔር ተወላጅ ሲሆን “ቀድሞም ሲደራጅ ይህን ታሳቢ ያደረገ ነበር” ብለዋል።

ሀሳባቸውን የሚቃረን የራሳቸው ሰው ከተገኘ ወዲያው ይገደል የነበረ ሲሆን ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንደ ሰው አንደማይቆጥሩና ራሳቸውን ፍጹም አድርጎ የሚያስቡ አረመኔ እንደሆኑ ገልዋል።

“እንደፈለጋችሁ መናገር ትችላላችሁ” ይባልና በየዋህነት የሚናገር ወታደር ካለ ቀን ተጠብቆ ርምጃ ይወሰድበታል።የኢትዮጵያን የጦር ኃይል ሙሉ በሙሉ የራሳቸው በማድረግ በብቸኝነት ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው የከፈቱት ጦርነት በጀግናው መከላከያ እየከሸፈ ነው።

እንደ 1983 ዓ.ም ለማድረግ አስበው ቢነሱም የገጠማቸው ከዛ የተለየ ሆኗል ነው ያሉት።ተንኮላቸው በቴክኖሎጂ ተደግፎ ያደገ መስሏቸው የመዘዙት ጦር ስለ ሀገሩ ነፍሱን በሚገብር ኢትዮጵያዊ ተቀልብሶ ራሳቸውን እየወጋ መሆኑን ተናግረዋል።

ጊዜ በተለወጠ መጠን ነገሮች ሁሉ አብረው እንደሚለወጡ ያልተረዱት በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደ አስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን የሚያስቡት ህወሓቶች የትናንትን ታሪክ ዛሬ ላይ ለመድገም ያስባሉ። በሀሰት ፕሮፓጋንዳና በገንዘብ በመደለል ሀገር ለማፍረስ ከንቱ ድካም መሆኑን እንኳን ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ጋላቢያቸው ሳይቀሩ ዛሬ 1983 ሳይሆን 2014 ነው ብለዋቸዋል።

ሀገር ለማፍረስና ለመዝረፍ የሚሰሩት አስከፊ ጭካኔ ያንገሸገሻቸው ኢትዮጵያውያን ትግስታቸው ተሟጦ በማለቁ ዛሬ ዳር እስከዳር ሆ ብሎ በመውጣት በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አዝማችነት የእጃቸውን እያገኙ ነው። በዚህም ነገ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፀሐይ ፍንትው ብላ ትወጣለች።